
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሽዋ ዞን የባሶና ወረና ወረዳ አሥተዳዳሪ በለጠ በኩረ በመስኖ ለማልማት ከታቀደው 1 ሺህ 60 ሄክታር መሬት ውስጥ 896 ሄክታር የሚኾነውን ማልማት እንደተቻለ ተናግረዋል። የኑሮ ውድነቱንም ለማረጋጋት በተቋቋመው የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር አማካኝነት ለሸማቹ 1 ሺህ 700 ኩንታል ምርት እንደቀረበም ነው የተናገሩት።
በሥራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ ከታቀደው 2 ሺህ 800 ሥራ ፈላጊዎች መካከል 507 ብቻ ነው ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው ብለዋል አቶ በለጠ። በማኅበራዊ ዘርፍ ደግሞ በዓመቱ ከ1 ሺህ 900 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው ተብሏል። ለእነዚህ ሁሉ ተግባራት እንቅፋት የኾነውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በመንግሥት የሰላም ጥሪን ጨምሮ የሕግ ማስከበር ሥራም እንደተሠራ ዋና አሥተዳዳሪው አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሰላም ባለመኾኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚሠራውን ሥራ አዳጋች እንዳደረገው ነው የተናገሩት። በግጭት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ በመረዳት ኅብረተሰቡም ለሰላም መስፈን የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
