
አዲስ አበባ: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባንኩ ሀገሪቱ ያላትን ሃብት ተጠቅማ መልማት በሚያስችላት በዚህ ዘርፍ በመሳተፉ በካፒታል ገበያ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ያደርገዋል ተብሏል። የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጫንያለዉ ደምሴ አማራ ባንክ ከባንክ ባሻገር ብሎ ሲነሳ ባንኩ በልዩ ልዩ ዘርፎች ተሳትፎ እንደሚያደርግ ለመግለጽ ነው፡፡ ይህ ስምምነትም ለዚህ ማሳያ ነዉ ብለዋል።
ባንኩ ይህንን አክሲዮን በመግዛቱ ላቅ ያለ ደስታ እንደሚሰማቸዉ ዋና ሥራ አሥፈጻሚዉ ገልጸዋል፡፡ ለሀገር ትልቅ ፋይዳ በሚኖረዉ የካፒታል ገበያ መሳተፋችን ለባንካችን እድገት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነዉ ያሉት። የኢትዮጽያ ሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያ (ካፒታል ገበያ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ.ር) አማራ ባንክ በኢትዮጵያ ሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያ መሳተፍ መቻሉ አስደሳች ነዉ ብለዋል።
ኩባንያዉ 25 በመቶ በመንግሥት በጀት እና ቀሪዉ በግል ተቋማት የተቋቋመ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ይህ ኩባንያ ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲኾኑ የሚያስችል እና በሌሎች ሀገራት ተሳታፊ እንዲኾኑ የሚያደርግ ነዉ ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ ሲቋቋም በኢትዮጵያ ካሉ ተቋማት መካከል የፋይናንስ ተቋማት የአክሲዮን አባል እንዲኾኑ ቅድሚያ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል። የአማራ ባንክም የዚህ ተጠቃሚ ኾኗል ነዉ ያሉት። አማራ ባንክ የገዛው አክሲዮን ባንኩ የሰነድ መዋእለ ነዋይ ባለቤት ኾኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉዑሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
