
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሽዋ ዞን የመኮይ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ ተጠናቅቆ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኾን ተገለጸ፡፡ በሰሜን ሽዋ ዞን የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ውኃ እና ኢነርጂ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ችሮታዉ ዠቃለ በከተማዋ የውኃ አቅርቦት ችግሩ ሰፊ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ኀላፊው እንደሚሉት በንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ማነስ ምክንያት የመኮይ ከተማ ነዋሪዎች ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ እየተገነባ የሚገኘው የመኮይ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ ፕሮጀክት በቅርቡ አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታው 38 ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ የተካሄደ መኾኑ የተገለጸ ሲኾን ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል፡፡ ለአገልግሎት የሚበቃው የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ የከተማውን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ከነበረበት 25 በመቶ ወደ 70 በመቶ እንደሚያሳድገውም ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ ሦስት የገጠር ቀበሌዎችን ጨምሮ በመኮይ ከተማ ያሉ ከ35 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አቶ ችሮታው ለአሚኮ አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
