523 ሺህ 520 ኩንታል ማዳበሪያ በማዕከለዊ መጋዝን እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ መግባቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

33

ፍኖተ ሰላም: መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተገዛው 894 ሺህ 120 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 523 ሺህ 520 ኩንታል ማዳበሪያ በማዕከለዊ መጋዝን እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ መግባቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ለዞኑ አርሶ አደሮች ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ እንደነበር ይታወሳል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ጎረፍ ቃውንቻ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ፀጋው ዘለቀ እና አለከኝ ተሻገር ባለፈው ዓመት ለመኸር እርሻ የሚያስፈልጋቸውን የአፈር ማዳበሪያ ባለማግኘታቸው ለከተፍኛ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ከ6 ሺህ እስከ 7 ሺህ ብር ድረስ መግዛታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ በዚህ ዓመት ኩንታል በ3 ሺህ 500 ብር እየቀረበላቸው መኾኑን ገልጸዋል።

በማዳበሪያ እጥረት ምክንያት የተሻለ ምርት የሚያገኙበት የበቆሎ ማሳቸውን ወደ ሌላ ሰብል እንደቀየሩ ያወሱት አርሶ አደሮቹ በዚህ ዓመት የእርሻ ማሳቸውን እያዘጋጁ ባሉበት ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ማዳበሪያ ማግኘታችን የተሻለ ምርት እንድናመርት ያስችለናል ብለዋል።
የእርሻ ማሳቸውን እያለሰለሱ ባሉበት ወቅት የአፈር ማዳበሪያ ማግኘታቸው የሰብል ምርታማነታቸውን እንደሚያሳድግላቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

የጃቢ ጠህናን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ ሞሴ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በወረዳው ከተመደበው 157 ሺህ 193 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 87 ሺህ ኩንታል የሚኾነው በገበሬዎች መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገብቶ ሥርጭት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ለወረዳው የቀረበውን የአፈር ማዳበሪያ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እና የአከራይ ተከራይ ውልን መሰረት በማድረግ በፍትሐዊነት እየተሠራጨ መኾኑን አብራርተዋል፡፡ የቀረበው ማዳበሪያ የዘር ወቅት ከማለፉ በፊት ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባው አሳስባል፡፡

የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተስፋየ አስማረ በበኩላቸው በዘንድሮው የመኸር እርሻ 250 ሺህ ሄክታር በዘር በመሸፈን 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ይህን ግብ ለማሳካትም 894 ሺህ 120 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ግዥ ከተፈፀመበት ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 523 ሺህ 520 ኩንታል በማዕከለዊ መጋዝን እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ67 ሺህ ኩንታል በላይ የሚኾነውን ወደ ወረዳዎች በማጓጓዝ 21 ነጥብ 5 በመቶ የሚኾነውን በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ተሰራጭቷል። በዞኑ ባለው ወቅታዊ የፀጥታ መደፍረስ የቀረበውን ማዳበሪያ በተገቢው ፍጥነት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ባለመኾኑ ሁሉም አካል ግብዓቱ በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ በመተባበር የዜግነት ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። መረጃው የአማራ ኮሙዩኒኬሽን ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ ሀገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄን አስጀመሩ፡፡
Next articleበሰሜን ሽዋ ዞን የመኮይ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ ተጠናቅቆ በቅርብ ቀን ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኾን ተገለጸ፡፡