
ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ ሀገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄን አስጀምረዋል። በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሚመራው ይህ ሀገር አቀፍ ንቃናቄ ለቀጣይ ስድስት ወራት ይቆያልም ተብሏል። “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” ንቅናቄው የዜጎች በንጹሕ እና በጤናማ አካባቢ የመኖር መብት ለማስከበር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
ንቅናቄው የተጠናከረ የአካባቢ ሕግን ተከባሪነት ለማረጋገጥ፣  ለሚመለከታቸው ባለድርሻ  አካላት፣ ለልማት ተቋማት፣ ለአጋር አካላት እና ለመላው ማኅበረሰብ የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከት በወጡ አዋጆች፣ አሠራሮች እና ደንቦች ዙሪያ ግንዛቤ ማጎልበትን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ብክለት በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። 
ኢትዮጵያም ይህን ችግር ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናዎነች ትገኛለች። ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በማስተባበር በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባለፉት አራት ዓመታት 32 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኝ ተክላለች ። ለዓለምም ምሳሌ ኾናለች ነው ያሉት።
መሰል ጥረቶችን ብታደርግም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ብክለት ችግሮች ተጋላጭ እየኾነች እንደምትገኝ የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ “ይህ ንቅናቄም የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከት የሚሠሩ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል” ብለዋል።
ለንቅናቄው ስኬታማነት ሁሉም እንዲተጋ አቶ ተመስገን ጥሪ አቅርበዋል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አንስተው ከቅንጅት ሥራ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ንቅናቄው በሁሉም ክልሎች ሲተገበር የፕላስቲክ፣ የአፈር፣ የድምፅ እና የውኃ ብክለቶችን ለመከላከል ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መኾኑን አመላክተዋል። እንድ ኢፕድ ዘገባ በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		