“ወሰናችን ተከዜ ነውና ከትግራይ ሕዝብ ጋር በመልካም ጉርብትና እንኖራለን” የቆራሪት ከተማ ነዋሪ

163

ሁመራ: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር “ቃልን በማክበር በዘላቂነት እግር መትከል” በሚል መሪ መልዕክት በዞኑ ከቆራሪት ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክሯል። በውይይት መድረኩም የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)፣ የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አዲሱ ማለፊያው ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የቆራሪ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች የከተማዋ ኅብረተሰብ የአካባቢያቸውን አንጻራዊ ሰላም በንቃት እያስጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ጠላታችን ሕወሓት እንጅ የትግራይ ሕዝብ ባለመኾኑ ከትግራይ ሕዝብ ጋር በመልካም ጉርብትና እንኖራለን ያሉት የከተማዋ ነዋሪዎች የአማራ ሕዝብ ዋጋ የከፈለበት የማንነት እና የወሰን ጥያቄ መንግሥት በሕግ የእውቅና ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

በከተማዋ በ2013 ዓ.ም በሰሜኑ ጦርነት በደረሰው ጉዳት የመልሶ ማቋቋም ሥራ ባለመከናወኑ የመብራት፣ የባንክ፣ የአንቡላንስ እና የኔትዎርክ አገልግሎት ከሦስት ዓመት በላይ በመቋረጡ እየተቸገሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ችግራቸውን መንግሥት እንዲቀርፍላቸውም ጠይቀዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ከፋኝ ብሎ ለበርካታ ዓመታት በመታገሉ ዛሬ ላይ ነጻነቱን አግኝቷል ብለዋል። በቀጣይም አንድነታችሁን በማጠናከር ነጻነታችሁን አጽንታችሁ ልትጠብቁ ይገባል ነው ያሉት።

በዞኑ በጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶች የመልሶ ማቋቋም ሥራ በመሠራቱ በበርካታ ቦታዎች የመብራት፣ የባንክ እና የኔትዎርክ አገልግሎት እንዲጀመር ተደርጓል ነው ያሉት። በቀጣይም በቆራሪት ከተማ የመብራት፣ የኔትዎርክ እና የባንክ አገልግሎት ለማስጀመር የክልሉ መንግሥት ከዞኑ አሥተዳደር ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ጠቁመዋል። የአማራ ሕዝብ የማንነት እና የወሰን እንዲሁም የዞኑ የበጀት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት በርካታ የመንግሥት ሠራተኞችን በዞኑ በመቅጠር ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ናቸው። የክልሉ መንግሥት የዞኑ ኅብረተሰብ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ እዲረጋገጥ የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አንስተው የአማራ ሕዝብ እውነተኛ የማንነት እና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አሁን የተገኘውን ነጻነት እና አንጻራዊ ሰላም አስጠብቃችሁ ልትዘልቁ ይገባል ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አዲሱ ማለፊያ ሁሉን አቀፍ አሸናፊነት የሚገኘው በሰላማዊ ትግል መኾኑን በመረዳት ሰላማችሁን እና አንድነታችሁን ልታስጠብቁ ይገባል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በአብሮነት፣ በመተባበር የሚኖር እና አንድነትን የሚያስቀድም ነው ያሉት አቶ አዲሱ ውስጣዊ አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንደ ኅብረተሰብ የሚጠበቅብንን ኀላፊነት ልንወጣ ይገባል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በዓመት ለዞኑ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከተማዋ ለሁሉም ነዋሪዎች ምቹ እንድትኾን እየሠራ ነው።
Next articleየፓርቲያቸውን ተልዕኮ በመፈፀም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ አባላት ገለጹ።