
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የነዋሪዎችን የኢኮኖሚ ደረጃ ማዕከል ያደረጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ መኾኑን ያስታወቀው የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ ትኩረት እንደተሰጠው አስታውቋል፡፡ ከሰው ተኮር ፕሮጀክቶች መካከል የ38 ቤቶች ግንባታ ተጠናቅቆ በቅርብ ጊዜ ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፉ የገለጹት የእምዬ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሰራዊት ቤዛ ናቸው፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እንዳሉት የተለያዩ ድርጅቶችን እና የማኅበረሰብ ተሳትፎዎችን በመጠቀም ተግባሩ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአምስቱም ክፍለ ከተሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማከናወን 10 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ያስታወቁት፡፡
ከተማ አሥተዳደሩ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ ቤት ለመገንባት በሚያመች መንገድ በከተማው ፕላን እንዲካተት መደረጉንም አስታውቋል፡፡ በቀጣይም የተለያዩ ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶችን እና ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ለእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት በትኩረት እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
