
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ እና አካባቢው የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በመፍታት የአካባቢውን ሕዝብ ሰላም በዘላቂነት ለመመለስ ያለመ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱ በአጣዬ ከተማ በሦስቱም ቀበሌዎች የተካሄደ ሲኾን የተዘጉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ወደ ሥራ በሚገቡበት ኹኔታ ላይም ምክክር ተደርጓል፡፡
በየቀበሌው የተደረገውን የሕዝብ ውይይት የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የኮማንድ ፖስቱ ኀላፊዎች መርተውታል። የመከላከያ ሰራዊት የ112ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር አዛዥ እና የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ኮሎኔል አሰፋ አየለ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሽ ዓለማየሁ እና የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ኤልያስ አበበ በጋራ በመኾን መድረኩን መርተዋል።
በውይይቱ የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበት እና ለአጣዬ ከተማ የፀጥታ ችግር ግንባር ቀደም ተዋናይ የኾኑ አጥፊዎች ተጠያቂ መኾን እንዳለባቸው ተገልጿል። በሁሉም ወገን በኩል ያሉ ጦርነት ደጋሾች ሊታረሙ ይገባልም ተብሏል። ሕዝቡ እርስ በእርሱ የተሳሰረ፤ የረጅም ዘመን የአብሮነት እሴት ያለው ሕዝብ መኾኑም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በመኾኑም በአጣዬ እና አካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከቤት እና ከንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች መመለስ እንዳለባቸው፣ የተዘጉ አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት፣ የግል እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ተከፍተው ኅብረተሰቡን ማገልገል እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
