
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመንግሥት ሠራተኞች በተሰማሩበት የሥራ መስክ በትጋት፣ በታታሪነት እና በታማኝነት እና መሥራት እንዳለባቸው ተጠይቋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል። ባለፉት ስምንት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችም ቀርበዋል። ወቅታዊ የሠላም መደፍረስ ያለበት ሁኔታ እና የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ የተሠራው ሥራ ለውይይት ቀርቧል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቻምላክ ገብረ ማርያም ተሳትፈዋል። አሁን ላይ ላጋጠመው ችግር ያለፉ ዓመታት ችግሮች በፍጥነት እና በዘላቂነት አለመፈታት መኾኑ ተነስቷል። የሚሰጡ መፍትሄዎችም ስክነት የተላበሱ አልነበሩም ተብሏል። አሁንም ችግሮች በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው ነው የተገለጸው። መንግሥትም ጥያቄዎችን በትዕግስት መስማት እንዳለበት ተመላክቷል። ግራ በመጋባት የሚነገሩ ቃላት እና የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚጎዳው ሕዝብን መኾኑንም መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። የመንግሥት ሠራተኞች ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
የውይይቱ ተሳታፊ እና የባሕር ዳር ከተማ የመንግሥት ሠራተኛ ታየ መላኩ በውይይቱ ከወትሮው በላቀ ሁኔታ የአገልጋይነትን ሥሜት ተላብሰን መሥራት እንዳለብን ተረድተናል ብለዋል። ለልማት መደናቀፍ በሰበብ አስባቡ አገልግሎት የማይሰጡ ሠራተኞች ይኖራሉ፤ ይህም መታረም አለበት ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ውይይቱ ያለፉት 8 ወራት የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሰላም ማስፈን ሥራዎችን የመገምገም ዓላማ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። የመንግሥት መዋቅሩም ከግጭት ስጋት ወጥቶ የተሻለ እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚደረግ ውይይት ነው። በቀጣይም የ60 ቀን ዕቅድ አውጥተን ለማልማት እና የተቀዛቀዘውን የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ለማጠናከር ነው ብለዋል።
ባለፉት ወራትም ሰላም ከማስፈን ጎን ለጎን የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን፣ ለ21 ሺህ የቤት ማኅበራት አባላት የግንባታ ፈቃድ መሰጠቱን፣ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በጀት ተመድቦ መሠራቱን እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ችግሮቹ ተለይተው የከንቲባ ችሎት መጀመሩን ነው ምክትል ከንቲባው የገለጹት። የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም የመንግሥት ሠራተኞች ታታሪ፣ ትጉህ እና ታማኝ ኾነው ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
