
ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል። ለወራት በዘለቀው ግጭት ምክንያት ከደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ላይም ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ እንደገለጹት በ2015/2016 የምርት ዘመን በዞኑ ከነበረው የግብዓት ችግር በተጨማሪ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአራት ሚሊዮን ኩንታል የምርት ቅናሽ ታይቷል፡፡
አቶ ኑርልኝ በዞኑ የተከሰተው ግጭት በገቢ አሠባሠብ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በዞኑ ሊሠበሠብ ከታቀደው 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እስከ መጋቢት አጋማሽ መሠብሠብ የተቻለው ከግማሽ ቢሊዮን ብር ያልበለጠ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይም ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል። “በግጭቱ ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዋና አሥተዳዳሪው በቀጣይ ወራት የዞኑን ማኅበረሰብ ሰላም ከማስጠበቅ በተጓዳኝ ባላፉት ወራት ዞኑ በግጭቱ ምክንያት በሁሉም የልማት ዘርፎች ያጋጠመውን ኪሳራ ለማካካስ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ማረጋጋት፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና ማኅበረሰቡ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾን በማድረግ ፍትሐዊ የጤና ተደራሽነት ሥርዓትን መዘርጋት የዞኑ ሌላው የትኩረት ማዕከል መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
