
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በኢትዮጵያ ከፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ ወደ አማራ ክልል በተደጋጋሚ መጥተው ምክክር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ከአሁን በፊት በጦርነቱ የተጎዳውን የደሴ ሆስፒታል ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ከርእሰ መሥተዳድሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአማራ ክልል አሁን ባለው ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል። የፈረንሳይ መንግሥት ከአሁን በፊት በአማራ ክልል በግጭት የደረሰውን ጉዳት የማገዝ ሥራ መሥራቱን አንስተዋል። በምግብ ዋስትና ላይ እየሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት አምባሳደሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብ አቅርቦት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ለአርሶ አደሮች የዘር ሥርጭት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር ቀጣይ በሚኖሩ ሥራዎች ላይም እንደሚመክሩ ነው የተናገሩት።መንግሥታቸው በአማራ ክልል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለተቸገሩ ወገንኖች የምግብ አቅርቦት እና በሌሎች ድጋፎች ለመድረስ ጥረታቸውን እንደሚቀጥልም አንስተዋል። የፈረንሳይ ካምፓኒዎች በአማራ ክልል ኢንቨስት በሚያደርጉት ሁኔታ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ዙሪያም መወያየታቸውን አስታውቀዋል። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ሥራ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ሥራዎች ማለቃቸውንም ገልጸዋል። የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት ለሀገር ትርጉም ያለው ቅርስ መኾኑን አንስተዋል። የፈረንሳይ መንግሥት በላሊበላ ላይ ያለውን ሸልተር በማንሳት ታሪኩን በጠበቀ መልኩ እንደሚሠራውም ገልጸዋል። መንግሥታቸው ለክልሉ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የግጭቱ መነሻ፣ ሂደቱን፣ ያስከተለውን ጉዳት እና በቀጣይ ስለሚወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ዙሪያ መወያየታቸውን አስታውቀዋል። የፈረንሳይ መንግሥት በአማራ ክልል ውስጥ ማድረግ ስለሚገባው ሰብዓዊ እርዳታ፣ የልማት ድጋፍ እና የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ነው የተናገሩት።
የአማራ ክልል ያለበትን ሁኔታ፣ ችግር፣ ያሉትን እድሎች እና ከተባባሪ አካላት ስለሚጠበቀው ድጋፍ ከሀገራት እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት አነስተኛ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ክልልን እውነታ ማስረዳት ከሀገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የበለጠ ያሻሽላል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። ሀገራቱ በሕዝቡ እና በክልሉ ላይ ያላቸው አስተሳሰብ የተስተካከለ ይኾናል፣ ይሄ ሲሆን በችግሩም፣ በመልካም ነገሮችም፣ ትክክለኛ አመለካከት ይኖራቸዋል፣ ይደግፋሉ፣ ይረዳሉ ነው ያሉት።
የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ በክልሉ መንግሥት በኩል ያለውን ዝግጁነት እና በሌላኛው ወገን እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን አስገንዝበናል ብለዋል። ለስምምነቱ በክልሉ መንግሥት በኩል እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎችን ማድነቃቸውንም አስታውቀዋል። የጦርነቱ አጀማመር፣ በአማራ ክልል ያስከተለው ጉዳት፣ ጦርነቱ የተቋጨበትን መንገድ፣ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች የሰላም ሁኔታ ለማረጋገጥ እና የሀገሪቱን የሰላም ሁኔታ ለማሻሻል የአማራ ክልል እየወሰደው ያለውን ኀላፊነት ማስገንዘብ ችለናል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ችግር ታሪካዊ ዳራውን እና ሕጋዊ መሠረት ባለው መንገድ መፈታት እንዳለበት መነጋገራቸውንም ገልጸዋል። የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ያላባቸው አካባቢዎች ምን ዓይነት ታሪካዊ ዳራ እንዳላቸው ማስረዳት ይገባናል ብለዋል። አካባቢዎቹ በምን ዓይነት አግባብ እንደነበሩ እና አሁንም በሕጋዊ መንገድ እንዴት መፍታት እንዳለብን በግልጽ አስገንዝበናል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ትክክለኛውን ነገር ለይተን አስረድተናል ብለዋል። በክልሉ ያለውን ግጭት ወደ ሰላም ለመመለስ የክልሉ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎችን መግለጻቸውን ተናግረዋል። የአማራ ክልል በሰላም እጦት ውስጥ እንዳለ፣ የሰላም እጦቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን እየጎዳው፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የገደበ መኾኑን፣ የሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱን እና የአማራ ሕዝብ የሚታወቅበትን ማኅበራዊ መስተጋብር በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ መኾኑን ማንሳታቸውን ነው የተናገሩት። ግጭቱ አንዲት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖም አስረድተናል ብለዋል።
የፈረንሳይ መንግሥት በአማራ ክልል ሰብዓዊ እና ቁሳዊ እርዳታዎች እያደረገ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የፈረንሳይ አምባሳደር እና መንግሥት በአማራ ክልል ማድረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ተወያይተናል ነው ያሉት። የፈረንሳይ መንግሥት የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጥገና እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የቅርሱን ቀደምት አሠራር እና ታሪኩን በጠበቀ መልኩ ለመሥራት ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
በደሴ ሆስፒታል ላይ የጥገና ሥራ መሥረታቸውንም ተናግረዋል። በግብርናው ዘርፍ በምርጥ ዘር አቅርቦት እና በምርምር እየደገፉ መኾናቸውንም አንስተዋል። በኢንቨስትመንት ላይ እየሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ከአማራ ክልል ጋር በልማት እና በሌሎች ጉዳዮች መሥራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ተወያይተናል ነው ያሉት። ውይይቱ ፍሬያማ መኾኑን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ አምባሳደሩ በአማራ ክልል በመረጃ ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖረኝ አድርጓል ማለታቸውንም ገልጸዋል።
ስለ አማራ ክልል የሚነገረው ነገር እውነታውን የሚያንጸባርቅ አይደለም፣ የአማራ ክልልን እውነታ አውሮፓ እና መላው ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ አለባችሁ ማለታቸውን፣ እርሳቸውም ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		