ከ23 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሐ ግብር ይፋ ኾነ።

57

ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከሃይኒከን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለሦስት ዓመት ተግባራዊ የሚኾን የፕሮጀክት መርሐ ግብር አስጀምሯል። የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የኑሮ ማሻሻል እና የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም ኀላፊ ይድነቃቸው ወንድአፈራው እንዳሉት ወርልድቪዥን ለ50 ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። አሁን ላይም ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚተገበር የ92 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል።

ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል ደራ፣ ፋርጣ እና ፎገራ ወረዳዎች የሚኖሩ 23 ሺህ 387 አርሶ አደሮችን በቀጥታ፣ 116 ሺህ 935 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል። የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ፣ የተሻሻሉ የግብርና ግብዓቶችን እና ቴክኖሎጅዎችን ማስተዋወቅ፣ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት እና የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ነው ኀላፊው የገለጹት።

በሃይንከን ኢትዮጵያ ሰስቴኔብሊቲ የውጭ እና የመንግሥታዊ ጉዳዮች ኀላፊ ፈቃዱ በሻህ እንዳሉት ሃይንከን ኢትዮጵያ የማኅበረሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል በሚደረገው የልማት ሥራ የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎችም ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። ከእነዚህም ውስጥ ለባሕር ዳር የሽንብጥ ጤና ጣቢያ ማስፋፊያ ግንባታ እና በሰሜኑ ጦርነት ለተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች የምግብ እና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

በሰሜን ውሎ ዞን የአርቢት እና ሮቢት ከተማ በጦርነት የወደሙት ጤና ጣቢያዎችን መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም 21 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ አሁን ለይ የተጀመረው ፕሮጀክት ያለምንም ችግር በተቀመጠለት ጊዜ ከታለመለት ዓላማ ላይ እንዲውል መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብት ሥራ፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መንግሥት ትኩረት የሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። ፕሮጀክቱ የክልሉ ዋነኛ ትኩረት የኾኑ ጉዳዮችን ለይቶ ወደ ሥራ መግባቱ ሰላምን ማስፈን እና የማኅበረሰቡን ጥያቄ መመለስ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥትም ድርጅቱ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዞኑ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ የደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
Next article“የአማራ ክልልን እውነታ ማስረዳት ከሀገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የበለጠ ያሻሽላል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ