በዞኑ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ የደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

24

ደሴ: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ከቀበሌ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ኮንፈረንስ ውጤታማ እንደነበር የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገልጿል። “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት የማጠቃለያ ኮንፈረንስ መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው በውይይቱ የተሳተፉት መሐመድ ሁሴን፣ ፋጡማ ሰይድ እና ከበደ ካሳ ብልጽግና ፓርቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ውህድ ፓርቲ ኾኖ ከተመሠረተ እና በምርጫ አሸንፎ ሀገሪቱን ማሥተዳደር ከጀመረ ወዲህ በዞኑ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል። መሠራት ያለባቸው ቀሪ የልማት ጥያቄዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

በቀጣይም በክልል ደረጃ ለሚካሄደው ኮንፈረንስ ዞኑን ወክለው የሚሄዱ አባላት የሕዝቡን ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ ሊያቀርቡ ይገባል ብለዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው ከቀበሌ ጀምሮ የተካሄደው ኮንፈረንስ ውጤታማ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ኀላፊው ፓርቲው በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ በጥንካሬ የሚነሱ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ይሠራል ብለዋል። በመድረኩ የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የኢንስፔክሽን እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን የሥራ አፈጻጸም ሪፓርት ቀርቦ ጸድቋል፡፡ በክልል ደረጃ በሚካሄደው ኮንፈረንስ ዞኑን ወክለው የሚሳተፉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ አባላት ምርጫም ተካሂዷል።

ዘጋቢ :-አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሁሉንም አገልግሎቶች በማስጀመር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎጃም ዞን አስታወቀ።
Next articleከ23 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሐ ግብር ይፋ ኾነ።