
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)  የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የዞኑን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የሰሜን ጎጃም ዞን በ2016 ዓ.ም ከምዕራብ ጎጃም ዞን ተከፍሎ የክልሉን ይሁንታ አግኝቶ የተቋቋመ ዞን እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡
ዞኑ ለተጠቃሚዎቹ በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት ታሳቢ ተደርጎ እንደተቋቋመም ተናግረዋል፡፡በዞኑ ውስጥ ያሉ ወረዳዎች ትርፍ አምራች ወረዳዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተከሰተው የፀጥታ ችግር ተጽዕኖ ካደረሰባቸው ዞኖች ውስጥ አንዱ እንደኾነም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ ዞኑ ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመኾኑ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት፣ በቋሚ ተክሎች እና በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርትም የታወቀ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡
በርካታ ትልልቅ ወንዞች የሚገኙበት ዞን በመኾኑ በመስኖ በማምረትም ወረዳው ሰፊ ሽፋን ያለው መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ 23 ሺህ 736 ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል።
ከግብዓት አቅርቦት አንጻር ዞኑ 1 ሚሊዮን 164 ሺህ 857 ኩንታል ማዳበሪያ ለመጠቀም አቅዷል፡፡ እስካሁንም 265 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቧል፤ 119 ሺህ 574 ኩንታል ማዳበሪያም ተሠራጭቷል። ቀሪውን ለማስገባትም ጥረት እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
ዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ ቢኾንም የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በፈጠሩት የፀጥታ ችግር ማኅበረሰቡ ለችግር ተጋልጧል፣ ፋብሪካዎች ሥራ አቁመዋል፣ ተቃጥለዋል በሌላ በኩልም አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ ክልል እንዳይመጡ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካዎች ኢኮኖሚውን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም ውድመት በማስተናገዳቸው ሥራ አቁመዋል፤ በዚህም የሥራ እድል ፈጠራው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ነው ያሉት፡፡
የፀጥታው ችግር የዞኑን የንግድ እንቅስቃሴ በመግታት ማኅበረሰቡን ተጎጅ አድርጓል፤ ዞኑ ማግኘት ያለበትን ገቢ በወቅቱ እንዳያገኝ አድርጓል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው፡፡የሕዝቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች መፍትሔ እንዳያገኙ በማድረግ የተጀመሩ የመንገድ እና የድልድይ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡ የግብርና ግብዓት በወቅቱ እንዳይደርስ በማድረግ በምርታማነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል፡፡
ከጤና አንጻር ከክልል ወደ ወረዳዎች መድረስ ያለባቸው ግብዓቶች እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ማኅበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ አንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ ዞኑ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማወያየት እና ለችግሩ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ አልሞ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ውስጥ የሚገኙ 10 ወረዳዎች በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ማኅበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እያገኘ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል ባደረጉት ጥረት የሰላሙ ጉዳይ መሻሻል አሳይቷል። ማኅበረሰቡም በተፈጠረለት መድረክ እና በተደረገ ውይይት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ የጤና ግብዓቶች በፍትሐዊነት ማድረስ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ከጤና መድኅን አንጻር በዞኑ 290 ሺህ 870 አባላት ተጠቃሚ መኾናቸውን የጠቀሱት ዋና አሥተዳዳሪው የፀጥታ ችግር በመኖሩ አባላቱ ደብተራቸውን ማደስ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ አሁን በተፈጠረው ሰላም 4 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ለማደስ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል ብለዋል።
ገቢ ከመሠብሠብ አንጻር በፀጥታው ችግር ምክንያት ተቋርጦ ቢቆይም በመጣው ሰላም 180 ሚሊዮን ብር መሠብሠብ ተችሏል ነው ያሉት። የእርሻ ግብር መሠብሠብ መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡
በዞኑ 479 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 400 ሺህ 970 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ቆይተዋል፡፡ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ ሌሎችን ትምህርት ቤቶች ለማስጀመርም ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ሁሉንም አገልግሎቶች በማስጀመር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት።
ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የሰላሙ ባለቤት መኾን እንደሚገባውም አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግም አመራሮች ትኩረት ሠጥተው እየሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ግጭቶችን በመፍጠር ሰላም ማምጣት አይቻልም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በጠረዼዛ ዙሪያ መምከር ተገቢ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ 361 በጽንፈኝነት የተሰማሩ አካላት ወደ ሰላም ተመልሰው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በሰላም እየኖሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		