በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን ያልተመጣጠነ ተጠቃሚነት ለማጥበብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

76

አዲስ አበባ: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፋይናንስ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ውይይት በብሔራዊ ባንክ እና የዓለም ባንክ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በዘርፉ የሴቶች ተሳትፎን የሚያሳድግ የኢትዮጵያ ፍይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትወርክ (ኒውፊን) በይፋ ተመሥርቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ምንም እንኳን አካታች የፍይናንስ ሥርዓትን ለመገንባት ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሠራ ቢኾንም በፍይናንስ ዘርፉ ያለው የወንዶች እና ሴቶች ተሳትፎ ትልቅ ልዩነት ያለው ነው ብለዋል። በፍይናንስ ተቋማት ሴቶች መሪ ቦታ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በብሔራዊ ባንክ ጭምር አናሳ መኾኑን ተናግረዋል። ይህንን ልዩነት ለመቅረፍ ደግሞ የፍይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትወርክ መመሥረቱ ጠቃሚ እንደኾነ ገልፀዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ተወካይ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶኒኣ ፔትሬስኩ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ አካታች የፍይናንስ ሥርዓትን ለመተግበር የምታደርገውን እንቅስቃሴ ይደግፋል ብለዋል። የሴቶች የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የፋይናንስ ተጠቃሚነታቸው ላይ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የፍይናንስ ተቋማት የተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳፋሪኮም የተረክ የሽልማት መርሐ ግብሩን አጠናቀቀ።
Next articleሁሉንም አገልግሎቶች በማስጀመር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎጃም ዞን አስታወቀ።