
ወልድያ: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ለከተማዋ ሕዝብ መድከም ብቻ ሳይኾን የሕይወት መስዋእትነት እየከፈሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በውጤታማነት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከኢንቨስትመንት አኳያ ኢንቨስተር እስከሚመጣ ከመጠበቅ ይልቅ የተሻሉ ኢንቨስተሮችን በመለየት ካሉበት ድረስ በመሄድ መረጃ እየሰጡ ውጤት ያለው ሥራ መሥራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ሥራ አጥነትን ለመቀነስ የወጣቱን የሥራ ፈጠራ ክህሎት እና ፍላጎት በመጨመር የአካባቢውን ሃብት እና እቅም በመጠቀም እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘቡት። 10 ሚሊዮን ብር በመመደብ በንብ ማነብ ሥራ እንዲሰማሩ ስለመደረጉም አስረድተዋል። በተጨማሪም 14 ሚሊዮን ብር በመመደብ በዶሮ እርባታ ለማሰማራት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከዓለም ባንክ በሚገኝ 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሸዶች እየተገነቡ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት። በፀጥታ ችግር ውስጥ ኾነውም 90 በመቶ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ መሠራቱን ተናግረዋል። የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል ሕጋዊ ንግድን በማበረታታት በሕገ ወጥ ንግድ የተሰማሩትን ወደ ሕጋዊ ለማምጣት እየተሠራ መኾኑን በመግለጫቸው አውስተዋል።
የኅብረት ሥራ ማኅበራት ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ከተማ አሥተዳደሩ ባለፈው ዓመት እና በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 15 ሚሊዮን ብር በመደገፍ ለከተማው ነዋሪ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ እየታገዙ መኾኑን ነው የገለጹት። የከተማ ግብርናን በማስፋትም ኅብረተሰቡ ከጓሮው አትክልት ማምረት ይችል ዘንድ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከመሠረተ ልማት አኳያ ከደብረ ገሊላ —መናኽሪያ—ጎንደር በር ያለው ዋናው አስፓልት ከቆመበት ውስብስብ ችግር በመውጣት ባለፈው ስምንት ወር የተሻለ የሥራ ክንውን እዲኖረው ኾኗል ብለዋል። ይሁን አንጂ የካሳ ክፍያ እና ከሦስተኛ ወገን የማጽዳት ሥራ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ከሼህ አሊ አላሙዲ አደባባይ እስከ ስታዲየም መግቢያ እና ከስታዲየም መውጫ እስከ ዋናው መንገድ ያለው የአስፓልት መንገድ ሥራም የተሻለ ክንውን ላይ ነው ብለዋል።
የ30 ሜትር የአስፓልት መንገድ ግምባታው ሁሉንም ክፍለ ከተማ የሚያገናኝ በመኾኑ የከተማዋን እድገት የሚያፋጥን ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። የካሳ ክፍያ እና ተለዋጭ መሬቶችን በመስጠት ቅሬታ እንዳይኖር ተደርጎ ስለመሠራቱም ነው ያረጋገጡት። ከትምህርት ቤት ግምባታ አኳያ የሦስት ትምህርት ቤቶች ግምባታ ተጠናቅቆ ሥራ ጀምረዋል ነው ያሉት። የከተማውን የመብራት አቅርቦት በማሻሻል ከፈረቃ አገልግሎት በማላቀቅ የከተማው ነዋሪ 24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት እንዲያገኝ ተደርጓል ነው ያሉት።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልነበሩ የከተማዋ ገጠር ቀበሌዎችም ተደራሽ ማድረግ መጀመሩን በመግለጫቸው አውስተዋል። የመብራት ችግሩ ሲቀረፍ የንፁህ መጠጥ ውኃ መቆራረጥ ችግሩም ስለመቀረፉ ነው ያስረዱት። ይሁን እንጂ የውኃ አቅርቦትን ከማስፋት አኳያ ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት እየተሠራ ነው ብለዋል። በከንቲባ ጉባኤ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ከተማው ላይ ሰላም እንዲመጣ መፍትሔው በሕዝብ እጅ በመኾኑ ሰላምን ከውስጥ መፈለግ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ከኅብረተሰቡ ጋር መግባባት ላይ ስለመደረሱ አረጋግጠዋል። ከከተማዋ ፀጋ አኳያ በአግባቡ ሥራ እንዳይሠራ እንቅፋቶች ዛሬም አሉ ብለዋል፡፡ በሊዝ የተሸጠን ቦታ አሸናፊዎች ክፍያ አንዳይፈጽሙ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው በመኾኑ ገቢውን መሠብሠብ እንዳልተቻለ ነው ያስገነዘቡት። ድርጊቱንም ኅብረተሰቡ ሊያወግዝ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!