
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከምንጊዜውም በላይ ትብብርና አንድነታችንን በማጠናከር የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም መጠበቅ አለብን ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ አራተኛው ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራም “ኢፍጣራች ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ትላንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የመሰባሰቢያና የአብሮነት ማሳያ በኾነው የረመዷን ወር በጋራ በማፍጠራችን ምሥጋናችን ላቅ ያለ ነው ብለዋል። በታላቁ ወር እያደረግን ባለው ፆም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝና በመደገፍ ሊሆን ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የተቸገሩ ወገኖችን ከማገዝ ባለፈ ከምንጊዜውም በላይ ትብብርና አንድነታችንን በማጠናከር የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም በመጠበቅ ሊኾን ይገባል ብለዋል። ለኢፍጣር ፕሮግራሙ መሳካት የተባበሩ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎችና የጸጥታ አካላትን አመሥግነዋል። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሡልጣን አማን፤ የኢፍጣር መርሐ ግብር የአንድነታችን እና አብሮነታችን ማጠናከሪያ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በታላቁ የረመዷን ወር ፆማችን ተቀባይነት እንዲያገኝ ዱአ ከማድረግ ባለፈ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት የድርሻችንን እናበርክት ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዚዳንቱ አማካሪና የታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር የበላይ አስተባባሪ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ፤ የረመዳን ፆም የመሰባሰቢያና የአብሮነት ወር ስለመሆኑ አንስተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የረመዷን ወር አንድነት የሚንጸባረቅበት፣ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበትና አብሮነት ይበልጥ የሚጠናከርበት መኾኑንም ገልጸዋል። በታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራም ከማፍጠር በተጨማሪ በቁርአን ውድድር ላሸነፉ ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!