
ፍኖተ ሰላም: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የኃይል አቅርቦትን ለመፍታት ሲሠሩ የነበሩ ፕሮጄክቶች መቋረጣቸውን የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አስታውቋል፡፡ የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አሥኪያጅ ዳኛቸው አስረስ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡ አካባቢው አስቸጋሪ የኾነ የጸጥታ ችግር ማሳለፉንም ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ችግር እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ 38 ባለሃብቶች ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ወስደው እያለሙ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ወደ ፓርኩ የገቡት ባለሃብቶች ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ያስመዘገቡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የጸጥታው ችግር እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ ወደ ፓርኩ የገቡ ባለሃብቶች በጥሩ የልማት እና የግንባታ እንቅስቃሴ ላይ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ ከነሐሴ 2015 ዓ.ም እስከ ኅዳር 2016 ዓ.ም በነበረው ግጭት ምክንያት ፕሮጄክቶች የሥራ እንቅስቃሴያቸውን አቁመው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ዋነኛ ችግር የኃይል አቅርቦት መኾኑን ያነሱት ሥራ አሥኪያጁ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሰብስቴሽን ሥራ ይሠሩ የነበሩ ተቋራጮች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራውን አቋርጠዋል ነው ያሉት፡፡ የኃይል አቅርቦት ችግሩን በከፊል በመፍታት ወደ ሥራ ተገብቶ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ ትልቁን ጥያቄ ይፈታል ተብሎ የታለመለትን የኀይል አቅርቦት ግንባታ አቋርጦታል ነው ያሉት፡፡ የፓርኩን የኃይል አቅርቦት ችግር በታሰበው ጊዜ ለመፍታት የነበረውን ጥረት እንደሚያዘገየውም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎም ተቋራጮች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ጥረት እየተደረገ መኾኑን አቶ ዳኛቸው ገልጸዋል፡፡
ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ገብተው በግንባታ እና በማምረት ላይ ባሉ ፕሮጄክቶች ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል ተፈጥሮ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ እየከፋ ሲሄድ በተለይም በግንባታ ላይ የነበሩ ፕሮጄክቶች ሥራቸውን ሲያቆሙ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው የነበሩ ወገኖች ከሥራ ውጭ ኾነዋል ነው ያሉት፡፡ በጥሩ የማምረት ሥራ ላይ የነበሩ ፕሮጄክቶችም መቸገራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የጸጥታ ችግሩ ጥሬ እቃ በሚያቀርቡ አርሶ አደሮች፣ ባለሃብቶች አና በመላው ማኅበረሰብ ላይ ጫና መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል ችሮችን መፍታት ይገባዋል ብለዋል፡፡ “ከሰላም በላይ ምንም ነገር የለም” ያሉት ሥራ አሥኪያጁ የሰላምን ዋጋ በውል ተረድቶ ችግሮችን መፍታት ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ጦርነቱ የሚቀጥል ከኾነ ግን እስካሁን ከደረሰው የከፋ ቀውስ እንደሚፈጠር ነው የተናገሩት፡፡ የተጀመሩ ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም ስለ ሰላም ሊሠራ፣ ሊመክር እና ችግሮችን በውይይት ሊፈታ ይገበዋል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!