ከ157 ሺህ በላይ ተማሪዎች በሰላም እጦቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

22

እንጅባራ: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል። የሰላም መደፍረሱ በትምህርት ዘርፉ ላይ በፈጠረው ጫና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥም 157 ሺህ 785 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ገልጿል። 382 የሚኾኑ ትምህርት ቤቶችም የመማር ማስተማር ሥራ ማቆማቸውም ተነግሯል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ቡድን መሪ አጥናፍ መከተ ክስተቱ የሕጻናትን የነገ ተስፋ የሚያጨልም እና በሀገር ላይ ተሻጋሪ ችግሮችን የሚያስከትል በመኾኑ የትምህርት ተቋማት የቀውሱ ሰለባ መኾን እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።

መንግሥት እና ሕዝብ እያደረጉ ባሉት የሰላም ጥረት የፀጥታ ሁኔታው መሻሻል በታየባቸው ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የመማር ማስተማር ሥራን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ቡድን መሪው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአካባቢው ሰላም መፈጠሩን ተከትሎ በሁሉም አካባቢዎች የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር
Next articleየኃይል አቅርቦትን ለማሟላት ሲሠሩ የነበሩ ፕሮጄክቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት መቋረጣቸውን የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገለጸ።