“በአካባቢው ሰላም መፈጠሩን ተከትሎ በሁሉም አካባቢዎች የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር

16

ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተፈጠረው ሰላም በአበርገሌ እና በጻግቭጂ ወረዳዎች ተዘግተው የነበሩ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታውቋል።

አቶ ጌታቸው ሀጎስ የጻግቭጂ ወረዳ 02 ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰላም እጦት የጤና ጣቢያ አገልግሎቱ ተቋርጦ በመቆየቱ በርካታ ሰዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠው ነበር ብለዋል። አሁን ሰላም በመኾኑ በቀበሌያቸው ያለው ጤና ጣቢያ በመከፈቱ መደሰታቸውንም ነው ያስረዱት፡፡ የተጀመሩ የሰላም ሥራዎች ተግባራዊ እንዲኾኑ እንደሚፈልጉም ነው የተናገሩት።

የጻታ ጤና አጠባበቅ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ተፈራ አባዩ ጤና ጣቢያው ከ17 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአገልግሎት ውጭ ነበር ያሉት ኀላፊው አሁን ግን በተፈጠረው ሰላም አገልግሎቱን በማዘመን እና ተቋሙን በማደስ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

አሁንም ያልተሟሉ የህክምና መሳሪያዎች ቢኖሩም ከአጋዥ ድርጅቶች፣ ከመንግሥት እና ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ የመብራት አገልግሎት በወረዳው አለመኖሩ ችግር እንደኾነባቸውም ጠቁመዋል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አሰፋ ነጋሽ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ለሦስት ዓመታት ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በአበርገሌ ወረዳ እና ጻግቭጂ ወረዳ በሁሉም ቀበሌዎች የጤና ተቋማት ሥራ የጀመሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገርም አስፈላጊ መሳሪያዎችን እየተሟላ ነው ብለዋል። የጤና ተቋማት ዓላማቸው የማኀበረሰቡን ጤና መጠበቅ ነው። ማኅበረሰቡም የጤና ተቋማትን በባለቤትነት ሊጠብቃቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሕገ ወጡ ቡድን ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠየቁ፡፡
Next articleከ157 ሺህ በላይ ተማሪዎች በሰላም እጦቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።