
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ከሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ስኬታማ ሕዝባዊ ውይይት መደረጉ ተገልጿል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ እና የኮር አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል አዘዘው መኮንን በመሯቸው ሕዝባዊ መድረኮች ላይ ኅብረተሰቡ ሰላም ፈላጊ መኾኑን አረጋግጧል።
በደብረ ማርቆስ ከተማና እና ጎዛምን ወረዳ ዙሪያ፣ በእነበሴ ሳር ምድር ወረዳ፣ በመርጡለ ማርያም ከተማ አሥተዳደር፣ በስናን ወረዳ እሮቡ ገበያ፣ በባሶሊበን ወረዳ የጁቤ ከተማና ዙሪያው፣ በደጀን ወረዳ ከተማው እና ዙሪያው ከሚገኙ ከመምህራን፣ ከመንግሥት ሠራተኛው፣ ከባጃጅ ትራንስፓርት ባለንብረቶች፣ ከነጋዴዎች፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍልች ጋር በወቅታዊ የክልሉ እና የዞኑ የሰላም ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።
በውይይቱም ማኅበረሰቡ ግጭቱ እንዲቆም ፍላጎቱ እንደኾነ ነው የገለጸው፡፡ በሕገ ወጡ ቡድን ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ አሳስበዋል። የክልሉን ሰላም እና ልማት ከሚያውኩ ሀሳቦች እና ድርጊቶች ሁሉም ታቅቦ የተሻለውን ምፍትሔ መፈለግ እንደሚያስፈልግም ነው የተብራራው፡፡
ለመነገድ፣ ለመማር፣ ለመሥራት እና በነፃነት ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ሰላም ወሳኝ ነገር በመኾኑ ሁሉም አካል ለሰላም መስፈን የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይገባዋል ብለዋል። የጎጃም ኮማንድፖስት ለአሚኮ በላከው መረጃ ውይይቱ በየደረጃው እስከታችኛው የቀበሌ አሥተዳደር ድረስ መደረግ አለበት ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች መናገራቸው ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!