ቢግ ዳታ ምንድን ነው?

116

ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቢግ ዳታ በቀላል አገላለጽ ትልቅ የመረጃ ስብስብ ነው፡፡ ከኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ እጅግ በርካታ መረጃ በየአንድ አንዷ ሴኮንድ ይመረታል፡፡ አንድ ዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ በአንድ ወር ውስጥ 40 ኤክሳባይት መረጃ በተለያየ መንገድ ወደ ሳይበር ዓለም ይለቃል፡፡ አንድ ኤክሳባይት መረጃ ማለት አንድ ሚሊዮን ቴራባይት መጠን ካለው መረጃ ጋር እኩል ነው፡፡

የፎርብስ መረጃ እንደሚጠቁመው 2 ነጥብ 5 ኤክሳባይት መረጃ በየአንድ አዳንዷ ቀን ይፈጠራል፡፡ ታዲያ የትኛው ነው ቢግ ዳታ? የሚለውን ለመወሰን አምስት መስፈርቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት መመደብ እንችላለን፡፡ እነዚህ መስፈርቶች መረጃው የሚኖረው መጠን፣ የመረጃው ፍጥነት፣ የመረጃው ብዝኀነት፣ የመረጃው ታማኝነት እና መረጃው የሚኖረው ጠቀሜታ ናቸው፡፡ መስፈርቶችን በመጠቀም መረጃዎችን አደራጅቶ ለማስቀመጥ የሚያግዙ የተለያዩ ማዕቀፎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ካሳንድራ፣ ሀዱፕ እና ስፓርክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ለቁጥር የሚታክት መረጃ እየተመረተ የሚገኘው ደግሞ በኢንተርኔት፣ በሳተላይቶች፣ በሴንሰሮች፣ በሬዲዮ ሞገድ፣ በጂፒ ኤሶች፣ በስልኮች፣ በድረ ገጾች፣ በሕክምና መሳሪያዎች እና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች አማካኝነት ነው፡፡ በእነዚህ ሥርዐቶች አማካኝነት የሚፈጠረው የመረጃ ፍሰት ጥርቅም በመፍጠር ላይ ይገኛል።

በየጊዜው ከሚፈጠረው መረጃ ግዝፈት አንጻር አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አንድን ጉዳይ ለመፈለግ፣ የመረጃዎችን ግንኙነት እና ተዛምዶ ለመተንተን፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ድምዳሜ ለመስጠት፣ መፍትሔ ለመጠቆም እና የወደፊቱን ነገር አስቀድሞ ለመተንበይ ቢግ ዳታ አገልግሎቱ የላቀ ነው፡፡
የአንድን ሰው ወይም ተቋም ፍላጎት፣ ባሕርይ፣ ማንነት እና ቀጣይ የሕይዎት ሂደት ከሚጋሩ መረጃዎች በመነሳት እና መረጃዎችን በማጤን መተንበይ ይቻላል፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የቴሌ ኮምዩኒኬሽን ኅብረት ቢግ ዳታ ውስብስብ ነገሮችን ለመፍታት የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂያዊ አቅሞችን የሚገልጽ እና ከተለመደው መረጃ ጋር ሲነጻጸር ፍጥነቱ እና ዓይነቱ ከፍተኛ የኾነ የመረጃ ጥርቅም ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር የሚገኘው ግሎባል ፐልስ የተባለ ተቋም ደግሞ የተደራጀ እና ያልተደራጀ የመረጃ መጠንን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ሀረግ እንደኾነ እና መረጃው ብዙ ከመኾኑ የተነሳ በተለመዱ የመረጃ ቋቶች እና መተግበሪያዎች ማደራጀት እና መተንተን አስቸጋሪ የኾነ የመረጃ ዓይነት ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ የሳይንስ ፋውንዴሽን በበኩሉ ቢግ ዳታን ሲያብራራ ትልቅ፣ መጠነ ሰፊ እና ውስብስብ ኾነው ከተለያዩ መሳሪያዎች፣ የኢንተርኔት መረጃ ልውውጦች፣ ኢሜሎች፣ ቪዲዮዎች እና ሌሎች ዲጂታል ምንጮች የሚገኝ የመረጃ ስብስብ ነው ይለናል፡፡ ጠቅለል ባለ መንገድ ሲገለጽ ቢግ ዳታ መጠኑ እጂግ ሰፊ እና ውስብስብ እንዲሁም በተበታተነ ወይም በተደራጀ መልኩ የሚገኝ የዳታ ዓይነት ነው፡፡ በግዝፈቱ እና ውስብስብነቱ ምክንያት ለማቀናበር እና ለመተንተን ለየት ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል፡፡

ለቢግ ዳታ ዋና ዋና ምንጮች የሚባሉት አራት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሰዎች የሚጠቀሙባቸው የዲጂታል መሳሪያዎች ለምሳሌ ስልክ፣ የድር አሰሳ እና ሌሎችንም በዚህ ስር መጥቀስ ይቻላል፡፡ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ያሉን ግንኙነቶች፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና የሥራ ማስታወቂያዎች ደግሞ ሌላ የምንጭ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከሴንሰሮች የሚገኙ እና ለዳሰሳ ጥናት በስልክ ከሚሞሉ መጠይቆች የሚገኝ መረጃም ለቢግ ዳታ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ቢግ ዳታ ለአንድ ሀገር ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል፡፡ ፈጣን የኾነ የመረጃ ትንተና እና ትንበያ ለመስጠት ይጠቅማል፡፡ የአብዛኞቹ ሀገራት የማክሮ ምጣኔ ሃብት መረጃ የሚወጣው በየወሩ ሲኾን የቢግ ዳታ መኖር እና ይህን ለመተንተን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር ግን የመረጃ ትንታኔን በጣም በሚገርም ፍጠነት ሰርቶ ለማቅረብ ያስችለናል፡፡

ለአንድ ሀገር ምርት እና ምርታማነት ቢግ ዳታ የሚጫወተው ሚና እጅግ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የቴሌ ኮምዩኒኬሽን ኅብረት እንደሚያመለክተው ያላቸውን መረጃ በተገቢ መንገድ ለውሳኔ ግብአትነት የሚጠቀሙ ተቋማት መረጃን ለውሳኔ ግብአትነት ከማይጠቀሙ ተቋማት አንጻር ምርታማነታቸው በስድስት እጥፍ በልጦ ተገኝቷል፡፡

ግሎባል ፐልስ በዘርፉ የተጠኑ ጥናቶችን በመጥቀስ በዓለም ላይ በ2005 የነበረው የዲጂታል ዳታ መጠን 150 ኤክሳባይት ሲሆን ይህ አሃዝ በ2010 ወደ 1 ሺህ 200 ኤክሳባይት እድጓል ይለናል፡፡ እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥም የዲጂታል ዳታ እድገት በ44 እጥፍ እንደሚያድግ ተተንብዮ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ይህን እያደገ የመጣን ቢግ ዳታ ለመተንተን የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔ የሚሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ደግሞ በዘርፉ ያሉ ኩባንያዎች እያቀረቡ ነው፡፡ ለአብነት ኦራክል የተባለው ኩባንያ ኦራክል ቢግ ዳታ ስፔሻል እና ግራፍ፣ ኦራክል ኢንተርፕራይዝ፣ ኦራክል ቢግ ዳታ ኤስ ኪው ኤል እና ኦራክል ቢግ ዳታ ዲስከቨሪ የተባሉ ለትንተና የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን አቅርቧል፡፡

ቢግ ዳታ ምንም እንኳን ጠቀሜታ ቢኖረውም ትላልቅ ተቋማት ቢግ ዳታን ተደራሽ ለማድረግ ያላቸው ፍላጎታቸው ደካማ መኾን፣ የግል መብት እና የዳታ ጥበቃ እና የዳታ ምንጭ ማንነት ጉዳዮች በዘርፉ ያሉ ፈተናዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ቢግ ዳታን የመጠቀም ሂደት የበርካታ ዘርፎችን ቅንጅት የሚጠይቅ በመኾኑ እነዚህን ዘርፎች ማቀናጀትም ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከጊዜ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ አሁን ላይ የስልክ ተጠቃሚው ቁጥር 85 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በመኾኑም ተጠቃሚዎች የሚፈጥሩት መረጃ እየገዘፈ መጥቷል፡፡ እድገቱ የሚፈጥራቸውን መልካም እድሎች ለመጠቀም መረጃን በተገቢው መንገድ መሰብሰብ፣ ማቀናበር እና መተንተን ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፦ https://www.oracle.com/big-data/what-is-big-data…

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማውገዝ በሰላማዊ መንገድ የሕዝብን ጥያቄዎች ለማስመለስ በጋራ መሥራት ይገባል” የሰሜን ወሎ ዞን
Next articleበሕገ ወጡ ቡድን ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠየቁ፡፡