“የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማውገዝ በሰላማዊ መንገድ የሕዝብን ጥያቄዎች ለማስመለስ በጋራ መሥራት ይገባል” የሰሜን ወሎ ዞን

18

ወልድያ: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። ባለፉት ስምንት ወራት ጽንፈኛው እና ዘራፊው ቡድን በዞኑ የፀጥታ ስጋት ፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ የመከላከያ ሠራዊት፣ የዞኑ እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር በጥምረት በወሰዱት እርምጃ አንፃራዊ ሰላምን ማስፈን ተችሏል ብለዋል። የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ከዞን አስከ ቀበሌ ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች በታቀደው ልክ ባይኾንም ለመሥራት ተችሏል ነው ያሉት።

ጽንፈኛው ቡድን በፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች መድረሳቸውን በመግለጫው ጠቅሰዋል። ከጤና ተቋማት አኳያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና መሳሪያ ወድሟል፤ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒት ተዘርፏል። 45 ሺህ 577 ሕጻፃናት የአልሚ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ቢኾንም አልሚ ምግቡን ማጓጓዝ ባለመቻሉ እና የተጓጓዘውም በጽንፈኛው በመዘረፉ የሕጻፃናቱ የምግብ ክትትል እንዲቋረጥ ኾኗል ብለዋል

43 የጤና ተቋማት ወድመዋል። አምስት ጤና ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ዝግ ኾነዋል። ሌሎቹም ሙሉ አገልግሎት ለመስጠት መስተጓጎል ተፈጥሮባቸው ነበር። በዚህ ሳቢያ 15 ሺህ 576 እናቶች በቤታቸው እንዲወልዱ ተገድደዋል። 13 ሴቶች በወሊድ ለሕልፈት ተዳርገዋል ነው ያሉት። 100 ትምህርት ቤቶቸ በመዘጋታቸው 29 ሺህ 700 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል። 15 ሺህ 600 ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን አቶ አራጌ ይመር አስረድተዋል።

49 ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጀምሮ እንዲቋረጥም ኾኗል ብለዋል። ከንፁህ መጠጥ ውኃ አኳያ ተጠግነው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ 404 የውኃ ተቋማትን ጽንፈኛው ቡድን ባለሙያዎች ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ በማድረጉ ኅብረተሰቡ በውኃ እንዲቸገር አድርጓል ነው ያሉት።

ከጋሸና- ላሊበላ – ብልባላ ያለው እና ከወልድያ- ጋሸና ያለው የአስፓልት መንገድ ሥራም በወቅቱ ለመጀመር አልተቻለም። አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የሚሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶችም ተቋራጮች በፀጥታ ስጋት ምክንያት በሙሉ እምነት ገብተው ለመሥራት እንዳልቻሉ ነው ያስገነዘቡት።
ከቱሪዝም አኳያ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ለማከናወን አልተቻለም። በዓመት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቱሪስት ቢጠበቅም ከ600 ሺህ በላይ ቱሪስት መምጣት አልቻለም ብለዋል። ከቱሪስት ገቢ አንፃር 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ቢታቀድም እስካሁን 17 በመቶ ብቻ ማሳካት እንደተቻለ አስረድተዋል። ከቱሪዝም ጋር የተቆራኘ ገቢ ያላቸው አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና አስጎብኝዎችም ለከፍተኛ ችግር እንደተዳረጉ በመግለጫቸው አውስተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው ከሥራ እድል ፈጠራ አኳያ በዞን ደረጃ 80 ሺህ ሥራ አጦችን የሥራ እድል ለመፍጠር ቢታቀድም ከእቅዱ ከ30 በመቶ ያልበለጠ ሥራ አጥን ወደ ሥራ ማሰማራት ስለመቻሉ ገልጸዋል። የውጤቱ መቀነስ ምክንያትም የፀጥታው ችግር የፈጠረው የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት፣ የግንባታ እና ሌሎች ለሥራ እድል ፈጠራ አመች ዘርፎች መዘጋታቸው ነው ብለዋል።

ባለፉት ስምንት ወራት በተፈጠረው የሰላም እጦት የግብርናም ይሁን የኢንዱስትሪ ውጤቶች አንደልብ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ የኑሮ ውድነቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል። የመንግሥት እና የሕዝብ ተቋማት ብረቶች ተዘርፈዋል። አራት አምቡላንሶችን ጨምሮ 10 የቢሮ ተሽከርካሪዎች በጽንፈኛው ቡድን ስለመቃጠላቸው ነው ያብራሩት። የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የአማራን ክልል ሕዝብ ጥቅም እና ጥያቄዎች የሚያስመልስ ሳይኾን የሕዝቡን ጥቅምና ጥያቄዎች እንዳይመለሱ አንቅፋት የፈጠረ፣ እንዳንደማመጥ፣ አንድነት አንዳይኖረን ለሌሎች የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ቀውስ የሚያስገባ በመኾኑ ማንኛውም የኅረተሰብ ክፍል የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማውገዝ እና በመምከር በሰላማዊ መንገድ የአማራ ክልልን ሕዝብ ጥያቄዎች ለማስመለስ በጋራ መሥራት እንዲቻል ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ቀረበ፡፡
Next articleቢግ ዳታ ምንድን ነው?