ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ቀረበ፡፡

42

ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ መልዕክት ከመጋቢት 18/2016 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት 100 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ከመጋቢት 18 ቀን 2016 ዓም ጀምሮ እንደሚካሄድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ለዓባይ ግድብ ከሀገር ውስጥ ቦንድ ግዥና ስጦታ፣ ከዲያስፖራ ቦንድ ግዥና ስጦታ፣ ከ8100 “ኤ” እና ከደረት ፒን ሽያጭ 931 ሚሊዮን 984 ሺህ 102 ብር መሠብሠቡ በመግለጫው ተመላክቷል።

መላው ሕዝብ ለግድቡ ድጋፍ በማድረጉ ከግንባታ ምዕራፍ ወደ ውኃ ሙሌት እና የኃይል ማመንጨት ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ነው የተነገረው፡፡ ግንባታው በጥቂት ወራት ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል። ኢፕድ እንደዘገበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሌሎችም ቦንድ የሚሸጡ የገንዘብ ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቦንድ ለመሸጥ ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀዋል። ግድቡ ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ ውኃ ይዟል፤ ኢትዮጵያውያን በቦንድ ሳምንቱ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ጥሪ ቀርቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከተማ ግብርናን በማስፋፋት ኅብረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next article“የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማውገዝ በሰላማዊ መንገድ የሕዝብን ጥያቄዎች ለማስመለስ በጋራ መሥራት ይገባል” የሰሜን ወሎ ዞን