የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ኅብረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

21

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ ግብርናን በማስፋት ኅብረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታውቋል። የዞኑ እና የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በከተማ የግብርና ሥራ ላይ የተሠማሩ አርሶ አደሮች የልማት እንቅስቃሴ ተጎብኝቷል። በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኙም በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የኃይለማሪያም ማሞ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ አበበ ካሳዬ ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ግብርና መምሪያ ኀላፊ መርሻ አይሳነው በከተማ አሥተዳደሩ 35 ሄክታር መሬት በከተማ ግብርና ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ይህም ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማ ግብርና አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል። ሥራው ስኬታማ እንዲኾን እና ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም ከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በከተማ ግብርና ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና መሰል ተግባራት ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ ስለኾነ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ ቀበሌዎች እና ክፍለ ከተሞች የተሠሩ የከተማ ግብርና ሥራዎች በተለያዩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተጎብኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ፋንታነሽ መሃመድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን አፋጣኝ ምላሽ ለመሥጠት የሚያስችል የከንቲባ ችሎት ተጀምረ።
Next articleከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ቀረበ፡፡