በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን አፋጣኝ ምላሽ ለመሥጠት የሚያስችል የከንቲባ ችሎት ተጀምረ።

43

ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ችሎቱ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸዉን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በተደራጀ መንገድ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አላማ ያደረገ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገልጸዋል።

በክፍለ ከተማ በይግባኝ ለችሎቱ የሚቀርቡ፤ ዉሳኔ ተሰጥቶ ሳይፈጸሙ የቆዩ እና ከባለጉዳይ በቀጥታ ለችሎቱ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። በፍርድ ቤት እየታዩ ያሉ እና ዉሳኔ ያገኙ ጉዳዮች በችሎቱ የማይታዩ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል።

ከንቲባዉ ስለ ጉዳዩ ዕዉቅና ካለው በችሎቱ በቀጥታ መልስ ይሰጣሉ። ማብራሪያ የሚፈለግ ጉዳይ ከኾነ ደግሞ የሚመለከተዉ ተቋም ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ የቀጠሮ ቀን የሚሰጡ ይኾናል። የባለጉዳዩን እና የተቋሙን ሃሳብ አገናዝበዉ ከንቲባዉ የመጨረሻ ዉሳኔ የሚሰጡ ይኾናል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አበበ ምንውየለት እንዳሉት የከንቲባ ችሎቱ ሳይፈቱ ለበርካታ ጊዜ የቆዩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ያግዛል።

ችሎቱ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠውን የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን በማይነካ መንገድ ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ ነው የገለጹት። ይህ ደግሞ አሥተዳደራዊ ጉዳዮች ወቅቱን ጠብቆ ባለመፈታታቸው ምክንያት የሚፈጠረውን የፍርድ ቤቶች መጨናነቅ ያስቀራል። የፍርድ ጥራትንም ያረጋግጣል።

የከንቲባ ችሎት መጀመሩ በአንድ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ ተቋማት ለማስፈጸም የሚባክነውን ጊዜ፣ ጉልበት እና የሚወጣውን ሃብት እንደሚያስቀር በችሎቱ የተሳተፉ ተገልጋዮች ገልጸዋል። በማኅበረሰቡ እና በመንግሥት መካከልም መተማመንን ይፈጥራል፤ ሙስናንም ይከላከላል ብለዋል።

በችሎቱ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ለዓመታት ሳይፈቱ የኖሩ ችግሮች ጭምር ተነስተው ታይተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር -ጎንደር ኮማንድ ፖስት 9 ሺህ ሕገ ወጥ የሽጉጥ ጥይት በቁጥጥር ስር አዋለ።
Next articleየከተማ ግብርናን በማስፋፋት ኅብረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።