የባሕር ዳር -ጎንደር ኮማንድ ፖስት 9 ሺህ ሕገ ወጥ የሽጉጥ ጥይት በቁጥጥር ስር አዋለ።

29

ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር -ጎንደር ኮማንድ ፖስት በሕገ ወጥ መንገድ ተጓጉዞ ለጽንፈኛው ቡድን ሊደርስ የነበረ ዘጠኝ ሺህ የሽጉጥ ጥይት በቁጥጥር ስር አውሏል። መነሻውን ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ያደረገው ዘጠኝ ሺህ የሽጉጥ ጥይት ባሕር ዳር ቀበሌ 14 ከነአዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኮማንዶና አየርወለድ ክፍለ ጦር ሻምበል አዛዥ ምክትል መቶ አለቃ ደጀኔ አበባው ተናግረዋል።

የጽንፈኛው ተላላኪ የኾኑት ምንይሉ መንግስቴ እና ደረጄ መርሻ የተባሉ የጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ነዋሪዎች ናቸው ጥይቱን ከጎንደር ወደ ባሕርዳር ቀበሌ 14 ልዩ ስሙ ልደታ ሰፈር ሲያዘዋውሩ የተያዙት። ሕገ ወጥ ጥይቱን ተቀብሎ ለጽንፈኛው ኃይል ለሚያደርሰው አየነው ፀሐይ ለተባለ ግለሰብ ጨለማን ተገን አድርገው ሲያስረክቡ ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል ላይ በኮማንዶ እና አየር ወለድ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሻምበል አዛዡ ምክትል መቶ አለቃ ደጀኔ አበባው ገልጸዋል።

እርጥቡ ምስጋናው ከሚባል ባለሃብት ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው የሚናገሩት የሕገ ወጥ ጥይቱ አዘዋዋሪዎች ከጎንደር ባሕር ዳር እስከሚገቡ ድረስ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጅ ብቻ ሲጠቀሙ እንደነበር ተደርሶበታል። ጥይቱን ለመጨረሻው የጽንፈኛው ተላላኪና አቀባይ አየነው ፀሐይ በማስረከብ ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

“የጽንፈኛውን ሕልም የማምከንና ዘራፊውን ቡድን የመደምሰስ ተልዕኳችንን በማጠናከር የባሕር ዳር ከተማና አካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ዝግጁነታችን ከመቼውም ጊዜ የላቀ ነው” ሲሉም ሻምበል አዛዡ ተናግረዋል። ዘገባው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት ወራት በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ በዞኑ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ውድመት ማድረሱን የደቡብ ወሎ ዞን አስታወቀ፡፡
Next articleበባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን አፋጣኝ ምላሽ ለመሥጠት የሚያስችል የከንቲባ ችሎት ተጀምረ።