
ደሴ: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ወራት በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ በዞኑ የመንግሥት ተቋማት ላይ ዘረፋ እና ውድመት እንዲደርስባቸው፣ ሕገ ወጥነት እንዲስፋፋ እና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ማድረጉን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያት ዋልታ ረገጥ አሥተሳሰብ እና ፅንፈኝነት ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ሁሉንም ነገር በኃይል ለማስፈጸም በፈለጉ ጽንፈኞች የማያዋጣ አካሄድ ክልሉ ወደ ግጭት ገብቷል ብለዋል።
በጽንፈኛ ኃይሉ ማኅበራዊ ተቋማት ወድመዋል ያሉት አቶ አሊ መኮንን በፀጥታ ችግሩ ምክንያት በዞኑ ከሚገኙ 1 ሺህ 208 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 57 ትምህርት ቤቶች አሁንም ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ አይደለም ነው ያሉት:: ዘራፊው ቡድን በርካታ የመንግሥት ተቋማት ላይ ዘረፋ እና ውድመት አድርሷል። ጽንፈኛ ኃይሉ የጤና ተቋማትን አውድሟል፣ የሕጻናትን ምግብ ዘርፏል፣ አምቡላንስ እንዲቃጠል አድርጓል ነው ያሉት።
ጽንፈኛ ኃይሉ በፈጠረው ግጭት በዞኑ የምርት እና የሰው እንቅስቃሴ እንዲገደብ፣ እገታ እና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እንዲበራከት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም አድርጓል። በተጨማሪም በክልል እና በፌዴራል መንግሥት የሚሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲሥተጓጎሉ ማድረጉን የገለጹት አሥተዳዳሪው በዞኑ ከተያዙ 9 የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ብቻ መኾናቸውን ነው በመግለጫቸው የጠቀሱት።
ይህን ያደረገው ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚለው ኃይል መኾኑንም ነው የተናገሩት። በመኾኑም የገጠመውን ችግር ለመቀልበስ ባለፉት ወራት በዋናነት በሰላም ማስከበር እና በልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ላይ በትኩረት ሲሠራ እንደነበር ተናግረዋል።
ሰላም ለማስከበር በተሠራው ሥራ በዞኑ አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በ15 ወረዳዎች እና ከተሞች ብቻ ተወስኖ የነበረው የመንግሥት አገልግሎት በ29 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ላይ ሰላም ማስፈን እና መንግሥታዊ አገልግሎት መጀመሩን ነው ያስታወቁት፡፡
የዞኑ ሰላም ወዳድ ሕዝብ መሰል የትግል አካሄድ የማያዋጣ እና ጥያቄዎች በሕጋዊ መንገድ መመለስ አለባቸው ብሎ የሚያምን በመኾኑ በማኅበረሰቡ ትብብር ሰላም ማስፈን ተችሏልም ነው ያሉት። ራሱ ሕዝቡ ለሰላሙ መታገል ጀምሯል ያሉት አስተዳደሪው በወረባቦ እና ሳይንት ወረዳዎች ማኅበረሰቡ የልማት ሥራ ላይ ማተኮር አለብን በሚል ፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን እየታገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከልማት እና ከመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች አንፃር በበጋ ከታቀዱ ተግባራት የበጋ መስኖ ስንዴ 35 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ በዞኑ 26 ሺህ ሄክታር እየለማ ነው ብለዋል፡ በዞኑ በ348 ቀበሌዎች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል፣ 990 አዳዲስ ተፋሰሶች እየለሙ ነው፣ 840 ሺህ አርሶ አደሮች ለ23 ቀን መሳተፋቸውን አንስተዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ፣ በልማት ትሩፋት እና የፍራፍሬ ልማት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በዞኑ 501 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዷል ያሉት አሥተዳዳሪው እስካሁን 331 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ መጋዘን ገብቷል ነው ያሉት፡፡ ከዚህም 260 ሺህ ኩንታል ከአርሶ አደሮች እጅ ደርሷል ነው ያሉት።
የማኅበራዊ ልማትን በተመለከተ 368 ሺህ አርሶ አደሮች የጤና መድህን አባል ኾነዋል፡፡ በዚህም 255 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ነው ያሉት። ገቢ አሰባሰብ ላይ በዞኑ በበጀት ዓመቱ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንም ጠቁመዋል። ገበያ ለማረጋጋት በተከናወኑ ተግባራት ዩኒየኖች እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት 222 ሚሊዮን ብር መድበው የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም በመግለጫቸው አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!