
ጎንደር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል። ዋና አሥተዳዳሪው ሰላምን በማረጋገጥ ልማትን የትኩረት ማዕከል ማድረግ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል። ይሁን እንጅ “በጽንፈኛ ኃይሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በልማት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል” ብለዋል።
በመግለጫቸውም ባለፋት ስምንት ወራት አለመረጋጋት የነበረ ቢኾንም በተሠራው ሥራ አሁን ላይ በአንጻራዊነት ሰላም ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል። ከሰላም ማስከበር ሥራው ጎን ለጎንም በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አሳውቀዋል። በግብርናው ዘርፍ በ2015/16 የምርት ዘመን 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲኾን በበጋ የመስኖ ሥራም 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ምርት እና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን በንቅናቄ ለማከናወን በተደረገው ጥረት 15 ሺህ ሄክታር መሬት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች እንደተሠራ አስረድተዋል። የግብርና ግብዓት በዚህ ዓመት ካለፈው ዓመት የተሻለ ለማቅረብ እየተሠራ ቢኾንም ዞኑ ካለው አቅም አንጻር ግን አሁንም መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ አመላክተዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው እንዳሉት ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በቀጣይ በሥራ እድል ፈጠራ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለ57 ሺህ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ነው ያስረዱት፡፡ አልሚ ባለሃብቶችም በዞኑ እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የጤና መድኅን የአገልግሎት አሰጣጥን እና የመድኃኒት አቅርቦት የተሟላ እንዲኾን በዞኑ እየተሠራ ካለው ሥራ በተጨማሪ ገቢያን ለማረጋጋት ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
አሁንም ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዳሉ ያነሱት አቶ ወርቁ ኃይለማርያም እነዚህ የሚነሱ ችግሮችን ለማስተካከል ዞኑ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ተናግረዋል። ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደትም ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ሰላማዊ አማራጭን በመከተል የተሃድሶ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሰላማዊ ሕይወት መግባታቸውን ዋና አሥተዳዳሪው አረጋግጠዋል።
የዞን አሥተዳደሩ የሕዝብ ጥያቄ የኾኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የአጭር እና የረዥም ጊዜ እቅድ አስቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝም በመግለጫው ተነስቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!