
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) የብልጽግና ፓርቲ እያጋጠሙት የሚገኙ በርካታ ተግዳሮቶችን ስንቅም ትጥቅም እያደረገ ፈተናዎችን እያሸነፈ ለሕዝብ የገባውን ቃል ለመፈጸም ይሠራል ብለዋል::
ቢሮ ኀላፊው የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የግማሽ ምርጫ ዘመን አፈጻጸም ግምገማ እና የቀሪ ምርጫ ዘመን ዋና ዋና የትኩረት ጉዳዮች ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ፓርቲው ያስመዘገባቸውን ስኬቶች እና ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በየደረጃው ባሉ የአባላት መድረኮች ለይቷል ብለዋል፡፡
ፓርቲው ከኅብረተሰቡ የተቀበለውን አደራ ለመፈጸም እና የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር፣ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በቀጣዮቹ ዓመታት ምላሽ ለመስጠት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ማማሩ ከኑሮ ውድነት፣ ከሥራ እድል ፈጠራ እና መሰል የመልካም አሥተዳደር እና የመልማት ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት “የብልጽግና ፓርቲ ለሰላም እና ደኅንነት ሥራዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ይሠራል” ሲሉም ተናግረዋል::
የሰሜን ሸዋ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሰዓዳ ኢብራሂም “የምንገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ከሰላም እና ከፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ በዜጎች መፈናቀል እና ሞት እያጋጠመ ነው” ብለዋል። ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች በእጅጉ የተወሳሰቡ አድካሚ ቢኾኑም ፓርቲው እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
በክልሉ የተፈጠረው ፈተና ፖለቲካው እንዳይሰክን አሉታዊ ጫናን እያሳደረ ነው ያሉት ኀላፊዋ ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታውን ተከትሎ የተፈጠረው የማይክሮ ኢኮኖሚ መዛባትም የማኅበረሰቡ አኗኗር ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ እና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ስለመኾኑም ገልጸዋል እነዚህን እና መሰል የማኅበረሰቡን ፈተናዎች እና ጥያቄዎች በቀጣዮቹ ጊዜያት ለመመለስ ፓርቲው እና አባላቱ በቁርጠኝነት ይሠራሉም ብለዋል::
የፓርቲውም የግማሽ ምርጫ ዘመን አፈጻጸም ግምገማ እና የቀሪ ምርጫ ዘመን ዋና ዋና የትኩረት ጉዳዮችን የሰሜን ሸዋ ዞን ማጠቃለያ መድረክ የዞኑ የፓርቲው አባል መንግሥት ሠራተኞች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል::
ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!