በሰላም መደፍረስ ምክንያት የመንግሥት አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩ አከባቢዎችን ሥራ ለማስጀመር እየሠራ መሆኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

39

ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል። ዋና አሥተዳዳሪው በመግለጫቸው ባለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ብሎም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፣ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም ተስተጓጉለዋል ብለዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው ጽንፈኛ ሲሉ የገለጹት ኃይል በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተንቀሳቀሰባቸው አከባቢዎች ሁሉ በንፁሃን ላይ ግድያ፣ የተደራጀ ዝርፊያ እና ማኅበራዊ ተቋማትን የማውደም ሥራ ሠርቷል ነው ያሉት። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በበጀት ዓመቱ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የመንገድ፣ የመስኖ፣ የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ለማስፋት ታቅዶ የነበረ ቢኾንም በቀውሱ ምክንያት በታቀደው ልክ መፈጸም እንዳልተቻለም ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን መደበኛ የልማት ሥራዎች እንዳይቆሙ እየተሠራ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በገቢ አሠባሰብ እና በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ተደራሽነት አበረታች ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው በሠሩት ሕግ የማስከበር ሥራ ለረጅም ወራት በጽንፈኛ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የነበሩ አከባቢዎችን በማስለቀቅ መደበኛ የመንግሥት አገልግሎት ለማስጀመር እየተሠራ እንደኾነም አቶ ቴዎድሮስ ገልፀዋል።

የፖለቲካ መሪው ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በማቀናጀት በሁሉም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አከባቢዎች ሕረተሰቡን የማወያየት እና የመንግሥት መዋቅር የመዘርጋት ሥራ እየሠራ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ኅብረተሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት እና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ በሚገባው ጉዳይ ላይ መግባባታቸውን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
Next article“የብልጽግና ፓርቲ ለሰላም እና ደኅንነት ሥራዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ይሠራል” ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)