
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNOHCHR) የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እና የአፍሪካ ኅብረት ዳይሬክተር ማርሴል አክፖቮ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እና የአፍሪካ ዳይሬክተር ማርሴል አክፖቮ በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እና የሰብዓዊ አያያዝ ዙሪያ መወያየታቸውን አስታውቀዋል። ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ ማንሳታቸውን ገልጸዋል። የግጭቱ ዋና ምክንያት በኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውንም ነው ያነሱት። የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በተመለከተ ያለውን ተነሳሽነት የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል።
ድርጅታቸው ፖለቲካዊ ተቋም አለመኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ለሰብዓዊ መብት ጥብቃ ትኩረት ያደርጋል ነው ያሉት። መንግሥት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሄደበት ያለውን ጥረት አድንቀዋል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ተጠያቂነት እንዲኖር መምከራቸውንም ገልጸዋል። ድርጅታቸው በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መኾኑንም ተናግረዋል። በግጭቱ ንጹሃን ዜጎች ከየትኛውም አካል ከለላ ሊሰጣቸው እና መጠበቅ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ባለፉት ዓመታት እና በአሁኑ ወቅት ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል። በሰሜኑ ጦርነት የደረሰውን ጉዳት አንስተው መወያያታቸውን ነው የገለጹት። አሁን ያለውን የአማራ ክልል ግጭት ያስከተለው ጉዳት በተመለከተም በዝርዝር መወያየታቸውን ተናግረዋል። በአማራ ክልል በተከሰተው ድርቅ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ መክረናል ነው ያሉት።
ድርቅ እና ግጭት ያስከተለውን ጉዳት ለመቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸውንም አስታውቀዋል። ከክልሉ መንግሥት ጋር መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች መወያየታቸውን ገልጸዋል። ሙያዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ነው የተናገሩት። ድርጅቱ ከአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ኮሚሽን እና የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መኾኑን ገልጿል ነው ያሉት።
ተቋሙ በአማራ ክልል ካለው ሰፊ ችግር አንፃር የሚጠበቅበትን አለመሥራቱን ማስገንዘባቸውንም ተናግረዋል። ወደ ፊት በትኩረት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል ነው ያሉት። በየጊዜው በመገናኘት በሰብዓዊ አያያዝ እና ድጋፍ ዙሪያ ለመምከር መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያድርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!