24

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የተሰማራው ኮማንድ ፖስት ጽንፈኛውን ቡድን ተከታትሎ በመያዝ ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ።

ደብረ ማርቆስ:- መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣናው የሚገኘው ኮር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ሙላው በየነ፣ በዘላቂነት የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ኦፕሬሽኑ ይቀጥላል ብለወዋል። በዞኑ የተሰማራው ሠራዊት ሬጅመንት አዛዦች እንደተናገሩት ሰሞኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሸበል በረንታ ወረዳ መርገጭ እና አካባቢው በጽንፈኛው ኃይል ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ47 በላይ ታጣቂዎች ሲደመሰሱ ከ20 በላይ ቆስለዋል። በተጨማሪም ጽንፈኛው ለጥፋት ዓላማው ሲጠቀምባቸው የነበሩ አንድ ፒኬ ኤም መትረየስ ከመሰል ጥይቱ ጋር እና ሰባት ኤ ኬ ኤም ተማርኳል ነው ያሉት።

የሬጅመንት አመራሮቹ ሻለቃ ኀይላይ ሃድጉ እና መቶ አለቃ አወል ያሲን እንደተናገሩት በአካባቢው የነበረው ጽንፈኛ ኀይል ለጥፋት ዓላማው ተባባሪ እንዲኾን በሸበል በረንታ አካባቢ ያለውን ኅብረተሰብ በማነሳሳት ከጎኑ እንዲሰለፍ የሞከረ ቢኾንም ኅብረተሰቡ ሳይቀበል በመቅረቱ ሕገ ወጡ ቡድን ኪሳራ እንደደረሰበት አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በቢቡኝ የተሰማራው የሠራዊት አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አሸናፊ ብርቄ እንዳሉት በቢቡኝ ወረዳ ድጎ ከተማ በአሰሳ ላይ በነበሩ የመከላከያ እና የክልሉ ጥምር የፀጥታ ኀይል ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሞከረው የጽንፈኛው ታጣቂ ኀይል ላይ በተወሰደበት ፈጣን አፀፋዊ እርምጃ ከ20 በላይ የጽንፈኛው ኀይል ሲገደሉ ከ15 በላይ ቁስለኛ ማድረግ ተችሏል። ቡድኑ ሲጠቀምበት የነበረ የጦር መሳሪያም በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።

በሰኞ ገበያ እና በናብራ አካባቢ በጽንፈኛው ኀይል ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ40 በላይ ታጣቂ ሲገደል በርካታው እግሬ አውጭኝ ብሎ እንደፈረጠጠ ተገልጿል። በቀጣናው የሚገኘው ኮር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ሙላው በየነ እንደገለጹት በጽንፈኛው ኀይል ላይ የተገኘው ድል የሕገ ወጡን ቡድን ከሰላም ወዳዱ የአማራ ሕዝብ መነጠል አስችሏል ነው የተባለው፡፡ ጽንፈኛው ኀይል የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በትጥቅ ትግል ነው እያለ ንፁሐንን አስገድዶ ለጥፋት ዓላማ የሚያውል፣ አግቶ ገንዘብ የሚቀበል፣ ንብረት የሚያወድም እና የሚያቃጥል፣ የሕዝብ እና የተቋም ንብረት የሚዘርፍ፣ ማዳበሪያ እንዳትወስዱ እኔ አመጣላችዋለሁ፣ ግብር አስቀርላችዋለሁ እያለ የክልሉን ሕዝብ ስቃይ እና የኢኮኖሚ ውድቀት እያፋጠነ የሚገኝ ወሮበላ ቡድን መኾኑን ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ ፊቱን እያዞረበት እንደሚገኝ የጎጃም ኮማንድ ፖስት መረጃ አመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁሉን ለማካተት እንነሳ” በሚል መሪ መልዕክት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን እያከበረ ነው።
Next articleየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ በሚገባው ጉዳይ ላይ መግባባታቸውን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።