
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በርካታ ጉዳት ደረሶበት የነበረው የ013 የቦያ ቀበሌ የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በትምህርት ሚኒስቴር እና በዓለም ባንክ የ21 ሚሊየን ብር ድጋፍ ግንባታው ተጠናቆ ርክክብ ተደርጓል።
የ013 ቦያ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ቀፀላ ትምህርት ቤቱ ቀደምት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ መደብ ላይ ተቀምጠው መማራቸውን አንስተዋል። የትምህርት ቤት ግንባታ ልዩ በመኾኑ “ዳግም በተወለድኩ” የሚያስብል መኾኑን አብራርተዋል። የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በየነ ምስጋን በጦርነት የወደሙ ተቋማትን ወደነበሩበት ለመመለስ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር አቅዶ እየሠራ መኾኑን አድንቀዋል።
እንደ አቶ በየነ ገለጻ ዛሬ ላይ ርክክብ የተደረገው 10 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሦስት ብሎክ እና የሴቶች እና የወንዶች መጸዳጃ ቤት መገንባቱን ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን ዓለም ባንክ እና የትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ለአማካሪ መሃንዲሶች በወረዳው ሕዝብ ሥም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ሰጠ ታደሰ ሕጻናት በተጎሳቆለ ትምህርት ቤት መማር የለባቸውም በሚል እሳቤ የትምህርትን ጥራት ለማምጣት የተሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስተር እና ትምህርት ቢሮው ከጉዳቱ እንዲያገግም ያደረጉትን ድጋፍ አመስግነው ኅብረተሰቡ ትምህርት ቤቱን በባለቤትነት ተረክቦ እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የሲቪል መሃንዲስ መስፍን ይልማ እንደገለጹት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ውድመት ከደርሰባቸው ሁለት መቶ ትምህርት ቤቶች መካከል የ013 የቦያ ቀበሌ የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ በኢትዮጵያውያን አርክቲክስቶች አማካኝነት ለቆላ እና ደጋው የሚኾን ዲዛይን በነፃ አሰርተው በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ማሠራት እንደተቻለ ገልጸዋል።
አቶ መስፍን ግንባታው 21 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እና ንጹህ መጠጥ ውኃ ለማሟላት ገንዘብ ማፈላለግ በተጨማሪ ባለድርሻ አካላትን ጭምር ውይይት እያደረጉ መኾኑን አብራርተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!