የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የአቅርቦት ችግሩን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

49

ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሱራፌል አየለ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከባሕር ዳር ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ መስመር የሕዝብ ማመላለሻ በማሽከርከር በሚያገኙት ገቢ ነው ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩት። እሳቸው እንደሚሉት በሰላሙ ወቅት ወደተለያዩ ከተሞች ሲንቀሳቀሱም ዋጋቸው የቀነሰ የግብርና ውጤቶችን እግረ መንገዳቸውን እያመጡ ይጠቀሙ እንደነበር ጠቁመዋል።

ለአብነት ወደ ደብረ ማርቆስ መስመር ሲጓዙ ቆጋ አካባቢ ሽንኩርት በተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚያገኙ እንደሚገዙ አስታውሰዋል። ስለኾነም ከራሳቸው አልፈው ጎረቤቶቻቸውን ጭምር ይደጉሙ እንደነበር ተናግረዋል። ወደ ደቡብ ጎንደር ሲንቀሳቀሱ ደግሞ የቲማቲም ምርት ከጉማራ እስከ ወረታ በስፋት እና በጥራት ከአርሶ አደሮች እጅ ስለሚያገኙ እንደማይቸገሩ አውስተዋል።

“አሁን ግን በፀጥታ ችግር ምክንያት የመንገዶች መዘጋት በመበራከቱ መኪው ከሥራ ውጭ በመኾኑ ገቢየም ቆሟል ፤ በሌላ በኩል አርሶ አደሮች ተረጋግተው ምርቱ ወደ ገበያ ማቅረብ ባለመቻላቸው የኑሮ ውድነቱ ፈትኖንናል” ነው ያሉት። የመንገድ መዘጋት ኹሉንም እንቅስቃሴ ያግዳል ያሉት አቶ ሱራፌል የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ መጨመር ከገቢ ማጣቱ ጋር ተደማምሮ ኑሮውን “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዳደረገባቸው አልሸሸጉም።

“እንደ ድሮው የተመጣጠነ ምግብ መሶባችን ላይ ማግኘት ቀርቶ ምሳ እና እራት በሰዓቱ ለማግኘት ተቸግርናል፤ እናም የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ስላልቻልሁ የማሳድጋቸውን ልጆች ለሌሎች ዘመዶች ለመስጠት እያሰብሁበት ነው” ብለዋል። አቶ አበበ ንጉስ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በክልሉ የፀጥታ ችግር ከመፈጠሩ በፊት አንድ ኪሎ ግራም ሽንኩርት 15 ብር፣ ድንች 12 ብር ይገዙ እንደነበር አስታውሰው ዛሬ ላይ ከ50 ብር የሚበልጥበት አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለዋል።

100 ኪሎ ግራም ጤፍ 8 ሺህ ብር ይገዙ እንደነበር የተናገሩት አቶ አበበ አሁን ላይ አንድ ኩንታል ጤፍ ወደ 14 ሺህ ብር አሻቅቧል ነው ያሉት። ለባሕር ዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች የወተት ምርት ከጢስ ዓባይ አካባቢ ይመጣልን ነበር ያሉት ወተት በማከፋፈል የተሰማሩት ወይዘሮ የሽጥላ አስረስ ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርት ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ሱቃቸውን ለመዝጋት ተገድደዋል። ምርቱን ማከፋል በማቋረጣቸው በተለይ ሕጻናት እና ሕሙማን መቸገራቸውን እየነገሯቸው እንደኾነም ጠቁመዋል።

“ሁሉም ነገር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው” የሚሉት ወይዘሮ የሽጥላ ከወራት በፊት 7 ብር የነበረው የዳቦ ዋጋም 12 ብር ገብቷል። 10 ብር የነበረው የውኃ ዳቦ ደግሞ 35 ብር ኾኗል ብለዋል። “5 ሊትር ዘይት 1100 ብር እንገዛለን” ያሉት ወይዘሮ የሺጥላ አንድ ኪሎ ግራም ጤፍ ከ100 እስከ 150 ብር በመድረሱ የለምለም እንጀራ ዋጋ 25ብር ደርሷል ነው ያሉት።

እንደ ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ምስር ያሉት ዋጋቸው በሰላሙ ጊዜ ከነበረው ጨምሯል። ስለኾነም ገቢያችን እና ወጪያችን ከፍተኛ ልዩነት አለው ብለዋል። በዚህም የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ከማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። አቶ ስላባት ቸኮል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በምጣኔ ሃብት በመሥራት በአሁኑ ወቅት መንግሥታዊ ባልኾነ ድርጅት ውስጥ ምጣኔ ሃብት ላይ እየሠሩ ይገኛሉ። እሳቸው እንዳሉት መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ አልያም ለመቆጣጠር የሰዎችን የገቢ ሁኔታ እያጣራ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች የሚስተናገዱበት ሱቆች በየቀበሌዎች ቢከፍት ይበጃል ብለዋል።

ከአፍሪካ እነ ሩዋንዳ፣ ኮትዲቯር፣ ናይጀሪያ፤ ከላቲን አሜሪካ ኩባ እና አርጀንቲና ልክ እንደኛው ኹሉ የውስጥ ችግር ገጥሟቸው በነበረበት ጊዜ ያጋጠማቸውን የኑሮ ውድነት እና ገበያቸውን ያረጋጉት ዝቅተኛ ነዋሪዎች የሚደጎሙበት ብሎም በቅናሽ ዋጋ ምርት የሚያገኙበትን ሱቆች በየአካባቢዎች በመክፈት ነው። ችግሩንም መቋቋም ችለዋል። ይህ ተሞክሮ ለእኛ ሀገር እና ክልልም ይሠራል ነው ያሉት ምሁሩ።

ምርት በማከማቸት ዋጋ እንዲንር ምክንያት በሚኾኑ ነጋዴዎች እና በሸማች እና አምራች መካከል በመግባት የኑሮ ውድነት በሚያስከትሉ ነጋዴዎች ላይ በቂ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል። ምሁሩ መሰረታዊ የሚባሉት ምርቶች ዋጋ ከፍ የሚለው ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር ባለመጣጣሙ መኾኑን አስታውሰው፤ አቅርቦትን በመጨመር ገበያው እንዲረጋጋ ማድረግ የመንግሥት ኀላፊነት ነው ብለዋል።

የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) ገበያውን ለማረጋጋት ችግሮች ጎልተው በሚታይባቸው እንደ ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ እና ወልድያ ከተሞች ባለሃብቶች፣ ዩኒዬኖች እና የሸማቾች ማኅበራት ከግብርና ምርቶች ጤፍ፣ ድንች፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ፍራፍሬ፣እንቁላል፣ ወትት እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በትስስር በአጭር ጊዜ ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ ተደርጓል ብለዋል። መሰል ሥራዎችን በመሥራት የኑሮ ውድነቱን በማርገብ ገበያውን ለማረጋጋት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ለአብነት የአንድ እንቁላል ዋጋ 14 ብር ደርሶ የነበር ሲኾን ገበያውን ለማረጋጋት በተሠራው ሥራ ወደ ስምንት ብር ማውረድ ተችሏል ነው ያሉት።

ኀላፊው እስካሁን የነበረውን የግብይት ሰንሰለት ሂደት ሲያብራሩ ደላላው ከአርሶ አደሩ ተረክቦ ለነጋዴዎች ያስረክባል፤ ቸርቻሪዎች ለጉልት ሻጮች ይሸጣሉ ብለዋል። በዚህ ሂደት ምርት በረዥም ሂደት ስለሚዘዋወር ገበያው እንዲራብ የሚያደርገውን የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር አርሶ አደሮች በቀጥታ ምርቱን የሚሸጡበት ሥርዓት እየተመቻቸ ነው ብለዋል። ይህም ገበያውን አረጋግቶ የኑሮ ውድነቱን እንደሚያረግብ ታምኖበት ለተግባራዊነቱ እየተሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ብርሃን ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች እና ሥራዎች አፈጻጸም ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
Next articleበሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰበት የ013 ቦያ ቀበሌ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቅቆ ርክክብ ተደረገ።