የደብረ ብርሃን ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች እና ሥራዎች አፈጻጸም ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡

17

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከከተማ፣ ከክፍለ ከተማ እና ከቀበሌ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች እና ሥራዎች አፈጻጸም ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡ የምክክር መድረኩ እየተካሄደ ያለው “ቃልን በማክበር በዘላቂነት እግር መትከል”በሚል መሪ መልዕክት ነው፡፡

የአማራ ክልል በይነ መንግሥታት ግንኙነት ቢሮ ኀላፊ ደስታ ተስፋው (ዶ.ር) የብልጽግና ፓርቲ ከሕዝብ ሥልጣኑን ከተረከበ ጊዜ አንስቶ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የሕዝቡን ችግር ነቅሶ በማውጣት ፈተናዎችን ከማሻገር አንጻር የበለጠ ኀላፊነት ወስዶ ፓርቲው እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው የክልሉ መንግሥት የሚስማማባቸው የተቆጠሩ ችግሮች መኖራቸውንም ዶክተር ደስታ አንስተዋል፡፡ ችግሮች እንዲፈቱ ሕዝቡን ከጎን በማሳለፍ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲ በኾነ መንገድ ምላሽ ለመስጠት መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ታጠቅ ገድለ አማኑኤል የደብረብርሃን ከተማ መሪዎች በራሳቸው አቅም፣ በልዩ ልዩ ሥልጠናዎች፣ ግምገማዎች እና በሥራ ላይ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ አቅማቸውን የማሳደግ ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የገለጹት፡፡ ያም ኾኖ ውስንነቶች ያሉበት በመኾኑ የሥራ ውጤታማነት ጉድለት ለመሙላት የሚያስችሉ ሥራዎች ይጠበቃሉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ የመሪዎቹ የመፈጸም እና የማስፈጸም ብቃትን ማሳደግ፣ ለሥራ ጥራት ትኩረት ማድረግ፣ የከተማው የፀጥታ ሁኔታ አሥተማማኝ እንዲኾን መሥራት እና የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በጊዜ ምላሽ መስጠት የሚችል መሪ መፍጠር በመድረኩ ጠንካራ ውይይት የሚደረግባቸው ሃሳቦች እንደኾኑም ነው የተገለጸው፡፡

ዘጋቢ፡- ገንዘብ ታደሰ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተፈጠረው የፀጥታ እና የሰላም እጦት በጤና ሥራ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል” የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር
Next articleየኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የአቅርቦት ችግሩን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡