
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተፈጠረው የፀጥታ እና የሰላም እጦት በጤና ሥራ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ገልጿል። በክልሉ ከተፈጠረው እና ወራትን ያስቆጠረው የፀጥታ ችግር በርካታ አካባቢዎች ላይ ጉዳት ከማስከተል ባለፈ የሰው ልጅ ህይዎት እንዲቀጠፍ እያደረገ ይገኛል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደርም ችግሩ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በአሥተዳደሩ በጽንፈኛው ኀይል እየተፈጠረ ባለው የፀጥታ ችግር በዚህ ወቅት ይከናወኑ የነበሩት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በተፈለገው መንገድ እየተከናወነ አይደለም።
ጽንፈኛ ኀይሉ ጉዳት ካደረሰባቸው ተቋማት ውስጥ የጤናው ዘርፍ አንዱ እና ዋነኛው ነው። በተቋማቱ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ከአሚኮ አዊኛ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው እንደገለጹት አሥተዳደሩ ላይ የጽንፈኛ ኀይሉ በፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ማኅበረሰቦች አስፈላጊውን ሁሉ አገልግሎት እያገኙ አይደለም ብለዋል።
በገጠመው የፀጥታ ችግር ለህክምና የሚያስፈልጉ የመድኃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ ለማቅረብ ከፍተኛ ፈተና ስለመኾኑ ኀላፊው ገልጸዋል። በአሥተዳደሩ ከጽንፈኛው ነፃ በኾኑ አካባቢዎች በቂ ባይባልም አገልግሎቶች እየተሰጡ መኾኑን ጠቁመዋል።
እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጽንፈኛ ኀይሉ 31 ጤና ኬላዎች፣11 ጤና ጣቢያዎች እና 3 ሆስፒታሎች ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲኹም በከፊል ከመዘረፋቸው ባለፈ ሕንፃዎቹ ፈርሰዋል ነው ያሉት። በአምስት የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ላይም የተለያዩ ከፍተኛ ጉዳቶች ደርሰውባቸዋል ብለዋል። የጤና ተቋማት ለየትኛውም አካል ሰብዓዊ አገልግሎት ያለልዩነት የሚሰጡ ቢኾንም በጽንፈኛው የደረሰባቸው ጉዳት ግን ዓለም አቀፍ ሕጎችን ሁሉ የጣሰ በመኾኑ መታረም እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት፡፡
ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት በሰላም እንጂ በጦርነት እና በግጭት አይደለም ያሉት ኀላፊው ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ሁሉ በውይይት እና በመነጋገር መፍታት ይገባዋል ብለዋል። ጽንፈኛ ኀይሉ ከመንግሥት የቀረበለትን የሰላም አማራጮች ተጠቅሞ ለሰላም እና ለልማት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። ሰላም ለሁሉም ነገር መነሻ ነው ያሉት አቶ አየለ ሰላም እንዲሰፍን የኅብረተሰቡ ድርሻ ከፍተኛ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰሎሞን ስንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!