“ሰላምን በማረጋገጥ ተገቢውን ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት የመንግሥት ሠራተኞች ኀላፊነት ሊኾን ይገባል” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት

19

ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኮማንድ ፖስቱ ከጎዛምን ወረዳ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል። የሰላም መደፍረስ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሥነ ልቦና ጫና እንደሚያደርስ በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል።

በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት የሰው ሃብት እና ቁሳዊ ወድመትን አስከትሏል። በአጭር ጊዜ መፍታት ካልተቻለ ኢኮኖሚን የቀለጠ የሚያዳክም እና ለባሰ ድኅነት የሚዳርግ መኾኑን በመረዳት የመንግሥት ሠራተኞችም በሰላሙ ጉዳይ ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ አናሳ መኾን፣ ተንቀሳቅሶ መሥራት አለመቻል፣ መፈናቀል እና ሌሎች የግጭት አባባሽ ምክንያቶችን መንግሥት ሊያስተካክልላቸው እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል። ሰላምን ለማምጣት መነጋገር እና መመካከሩ ተገቢ ስለመኾኑም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ቢሮ ኀላፊ ሀይሌ አበበ የተዛቡ አመለካከቶችን በማረም ወደፊትም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መተጋገዝ እና መተባበር እንዲሁም ሀገራዊ ሁኔታንም መረዳት ከመንግሥት ሠራተኛው የሚጠበቅ መኾኑን አስረድተዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋየ በላይ መንገድ በመዝጋት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ ያለውን አካል ልናወግዘው ይገባል ብለዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን ሰላም የአንድ አካል ብቻ አለመኾኑን በመረዳት ያልተገባ ወሬ እና አሉባልታ ከሚነዙ አካላት በማራቅ ተገቢውን ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የጎንደር አካል ድንበሩም ተከዜ መኾኑን በዞኑ የሚገኙ የኢሮፕ እና የኩናማ ብሔረሰብ ተወላጆች ተናገሩ።
Next article“የተፈጠረው የፀጥታ እና የሰላም እጦት በጤና ሥራ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል” የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር