የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የጎንደር አካል ድንበሩም ተከዜ መኾኑን በዞኑ የሚገኙ የኢሮፕ እና የኩናማ ብሔረሰብ ተወላጆች ተናገሩ።

126

ሁመራ፡ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር “አብሮነት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት በዞኑ ነዋሪ ከኾኑት የኢሮፕ፣ የኩናማ እና የትግራይ ብሔር ተወላጆች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኩናማ ብሔር ተወላጅ እና የኩናማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዩሐንስ ባዩ በ1923 ዓ.ም ቃብትያ ሁመራ ወረዳ በድሮ ሰሟ እንባድርኩታን በአሁን ስሟ አዲጎሹ ቀበሌ መወለዳቸውን አንስተዋል። ሀገራቸውን በወታደርነት እንዳገለገሉ ያነሱት አቶ ዮሐንስ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በጎንደር ግዛት በወገራ አውራጃ የሚተዳደር ሕዝብ እንደነበር ተናግረዋል። ተከዜ የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ወሰን መኾኑን አንስተው ተወልደው ባደጉበት ሀገር ከሕዝባቸው ጋር በፍቅር እና በመተሳሰብ እየኖሩ እንደኾነ አስገንዝበዋል።

ሌላኛው በውይይቱ ላይ የተገኙት ትውልደ ሱዳናዊው የገዳሪፍ ተወላጅ ሞሳ ኢሳ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለ40 ዓመት ነዋሪ መኾኑን አንስቶ በሕወሓት የአገዛዝ ዘመን የቀበሌ መታወቂያ በመከልከሉ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንዳልተቻለ እና እንግልት ይደርስበት እንደነበር አስታውሷል።
ከዞኑ ሕዝብ የነጻነት ማግስት በሕዝቡ መልካም ፈቃድ እና አስተባባሪነት የቀበሌ መታወቂያ አግኝቶ በነጻነት እየኖረ መኾኑን ተናግሯል። ኅብረ ብሔራዊነትን በጠበቀ መልኩ ለውይይት በመጠራታቸው ደስተኛ መኾናቸውን አንስተው የውይይቱ መካሄድ መቀራረብን እና እርስ በእርስ መደጋገፍን የፈጠረ ነው ብለዋል። ከነጻነት በፊት በዞኑ የሚገኙ ብሔረሰቦች የቀበሌ መታወቂያ ተነፍገው ይቸገሩ እንደነበር የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊዎች በውይይቱ ላይ ያገኙትን መልካም ነገር ወስደው ሕዝብን ለማቀራረብ በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። የዞኑ አሥተዳደር በአካባቢያቸው የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት በቋንቋቸው እንዲማሩ እንዲያመቻችላቸውም ጠይቀዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የአማራ ክልል መንግሥት በስሩ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎ የያዘ እና የአሥተዳደር ሥልጣን የሰጠ ለሌሎች ክልሎችም አርዓያ የሚኾን ነው ብለዋል። በክልሉ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብም አቃፊ በመኾኑ በውስጡ የሚገኙ የኢሮፕ ፣ የኩናማ እና የትግራይ ብሔር ተወላጆችን አቅፎ ይዟል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ የኩናማ እና የኢሮፕ ቀበሌ ነዋሪዎች የአማራ እና የትግራይ ድንበር ተከዜ መኾኑን በመድረኩ በመናገራቸው አመሥግነዋል። የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነቱን ካገኘ ማግስት ነጻነት ማግኘታችሁን ያነሳችሁ በመኾኑ ከመንግሥት ጎን ኾናችሁ ልትሠሩ ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ከሌሎች ክልሎች በተለየ ለብሔረሰቦች በዞን እውቅና የሰጠ ክልል በመኾኑ በወልቃይት ጠገዴ የምትኖሩ ብሔረሰቦች መብታችሁ የበለጠ እንዲከበር ይሠራል ነው ያሉት።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ኅብረ ብሔራዊነትን በመገንባት ወንድማማችነትን ለማስቀጠል ያለመ ውይይት መካሄዱን አንስተው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ማንነቱን በሕግ ለማጽናት የታገለ በመኾኑ የሌሎች ብሔረሰቦችን መብት የሚያከብር እንደኾነም ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በዞኑ የሚገኙ የኢሮፕ እና የኩናማ ብሔረሰብ ተወላጆች የቀበሌ መታወቂያ ተከልክለው ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው ከነጻነት ማግስት የዞኑ አሥተዳደር በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ችግራቸውን መቅረፍ እንደተቻለም አንስተዋል።

በቀጣይ በአካባቢያቸው ያለውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍ እንደሚሠራ ጠቁመው ትምህርት ቤቶች ተከፍተው በቋንቋቸው እንዲማሩ ይደረጋል ብለዋል። ዞኑ በውስጡ የሚገኙ ብሔረሰቦችን መብት በማክበር በልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። በሀገር ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት አግላይነትን ማስቀረት እንደሚገባ በውይይቱ ተመላክቷል።

ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በደም የተከበረውን በሕግና በላብ ለማጽናት ያለ እረፍት እየሠራን እንገኛለን” አሸተ ደምለው
Next article“ሰላምን በማረጋገጥ ተገቢውን ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት የመንግሥት ሠራተኞች ኀላፊነት ሊኾን ይገባል” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት