
ሁመራ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር ባለፉት ስምንት ወራት በዞኑ የተከናወኑ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የዞኑ አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ዞኑ ከነጻነት ማግስት ያለበጀት የሚንቀሳቀስ ቢኾንም የሰመረ የመንግሥት እና የሕዝብ ግንኙነት በመፍጠሩ በሕዝብ ተሳትፎ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የቤተ መጽሐፍት ግንባታ፣ ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኙ የመንገድ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ በተለይም በ2016 በጀት ዓመት የአውራ ወረዳን ከዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የሚያገናኝ 60 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ በሕዝብ ተሳትፎ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል። ከአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ጋር በመተባበር በቃብትያ ሁመራ ወረዳ የአጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት እየተገነባ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ለዞኑ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተው የዞኑ ሕዝብ የጤና መድኅን ተጠቃሚ እንዲኾን በበጀት ዓመቱ በቁርጠኝነት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዞኑ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ከአስር በላይ ወንዞች መኖራቸውን አንስተው በበጋ የመስኖ ልማት፣ በነባር 5 ሺህ 285 ሄክታር እና በአዲስ የመስኖ ልማት ከ239 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ የመስኖ ልማት 4 ሺህ 958 አርሶ አደሮች ተሳታፊ መኾናቸውን ገልጸው 214 ሺህ 850 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደተቻለም ጠቁመዋል። አቶ አሸተ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ችግር በዞኑ በግብርና ግብዓት እና በነዳጅ አቅረቦት ላይ ችግር መፍጠሩንም ገልጸዋል። የዞኑ ኅብረተሰብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም እያስጠበቀ ይገኛል ያሉት የዞኑ አሥተዳዳሪ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በአብሮነት የሚያምን በመኾኑ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በአብሮነት ይኖራል ብለዋል።
በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ ችግር የአማራ ሕዝብ የወሰን እና የማንነት እንዲሁም ሌሎችም ጥያቄዎች ምላሽ እንዳያገኙ እንቅፋት የሚፈጥር ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ጥያቄዎች የሚፈቱት በመሳሪያ ሳይኾን በንግግር እና በውይይት በመኾኑ ሁሉም የሰላምን አማራጭ ሊያስቀድም እንደሚገባ ተናግረዋል። በዞኑ እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በቁርጠኝነት እየሠራ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!