“በዞኑ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ በሰሜኑ ጦርነት ተቋርጠው የነበሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ተችሏል” ዲያቆን ሸጋው ውቤ

33

ደባርቅ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ባለፉት 8 ወራት በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር በዞኑ የተፈጠረው አሉታዊ ተጽዕኖ፣ ከችግሩ ለመውጣት በተከናዎኑ ሥራዎች፣ ዞኑ አሁን የሚገኝበት ነባራዊ ሁኔታ እና ወደፊት ምን ይጠበቃል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው በመግለጫቸው “የሰሜኑ ጦርነት ካደረሰብን ችግር ሳናገግም ለሌላ ውድመት እና ጥፋት ሊዳርግ የሚችል ግጭት ውስጥ ነው የገባነው” ብለዋል። አሥተዳዳሪው ጽንፈኛ ሲሉ የጠሩት ኃይል “በክልሉ ብሎም በዞኑ የሚፈልገውን ምኞት እና ፍላጎት ለማሳካት ሕዝባችንን ሰላም በመንሳት አካባቢያችን ተረጋግቶ ወደ መደበኛ የልማት ሥራው እንዳይመለስ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ያደረገበት ሁኔታ እንደነበር የሚታወስ ነው” ብለዋል።

አሥተዳዳሪው የተፈጠረው የፀጥታ ችግር መደበኛ የመንግሥት ተግባራትን ባቀድነው ልክ እንዳንፈጽም፣ ተጀምረው የቆሙ የልማት ሥራዎችን እንዳናስቀጥል፣ የግብርና፣ የጤና እና የትምህርት ግብዓትን በተገቢው መንገድ እንዳናቀርብ መንገድ በመዝጋት፣ በመዝረፍ እና ግድያ በመፈጸም መንግሥታዊ ተግባራትን እና ሕዝቡ የሚያቀርበውን የልማት ጥያቄ ማሳካት እንዳይቻል ትልቅ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን አብራርተዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው ዲያቆን ሸጋው ከዞኑ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በተለይ በቱሪዝም ዘርፉ የተሻለ እንቅስቃሴ የነበረበት ነው ካሉ በኋላ ቀደም ብሎ በሰሜኑ ጦርነት አሁን ደግሞ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው መሠረታዊ ችግር እንደገጠመው አንስተዋል፡፡
በጥቅሉ ነጻ የምርት እና የጉልበት እንቅስቃሴ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ የፀጥታ ችግሩ ከፍተኛ መስተጓጎል የፈጠረ ነበር ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው። ዲያቆን ሸጋው “ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በሚፈለገው ልክ ባለመመለሳቸውም ማኅበረሰቡ ለምን የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው” ብለዋል። ነጻ የምርት እንቅስቃሴ በመገደቡ እና ሕዝቡም የሚፈልገውን አገልግሎት እና አቅርቦት እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ በፀጥታ ችግሩ ምክንያት ችግሮችን መቋቋም፣ መፍታት እና አቅርቦቱን ማሟላት ባለመቻላችን ሕዝቡ ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና ለከፍተኛ ምሬት የተጋለጠበት ነባራዊ ሁኔታ ነበር ብለዋል።

“ይህንን መሠረት በማድረግ ሕዝባችንን ስናወያይ ፍላጎቱ ሰላም፣ ልማት፣ ማኅበራዊ አገልግሎት ሳይቋረጥ ማግኘት፣ ነፃ የምርት እንቅስቃሴ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ማግኘት ነው” ያሉት አሥተዳዳሪው ሕዝቡ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን እያወገዘ መንግሥት ሕግ ያስከብር የሚል ጽኑ አቋም ይዞም ከጎናችን የቆመበት እና የጽንፈኛውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ አምርሮ የጠላበት እና የታገለበት ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።

አሥተዳዳሪው እንዳሉት በዞኑ ቅድሚያ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለመነጋገር እድል በመሰጠቱ ከ500 በላይ ታጣቂ ኀይሎች በሰላም እጃቸውን ለመንግሥት ሰጥተዋል፡፡ የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው ከሕዝቡ ጋር ሰላማዊ ሕይወታቸውን እየቀጠሉ ናቸው ብለዋል። የጽንፈኛ ኃይሉን እንቅስቃሴ ለመገደብ እና ለማምከን እንዲኹም ዞናዊ የሰላም ሁኔታው እንዲሻሻል ብሎም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በተሠራ ሥራ ዞኑን ሰላም ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም ኹሉም የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ፣ በሰሜኑ ጦርነት ተቋርጠው የነበሩ የመንገድ እና የድልድይ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ፣ ሁሉም ማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ፣ የመልካም አሥተዳደር እና የፍትሕ ተቋማት ተግባራቸውን እየፈጸሙ ያሉበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

በዞኑ አንጻራዊ ሰላም አለ ብንልም ጽንፈኛ ኃይሉ የጥፋት ፍላጎት የለውም ብሎ ማስቀመጥ አይቻልም ያሉት አሥተዳዳሪው ቀጣይ ሥራ ይጠይቀናል ብለዋል። ስለኾነም አካባቢያችን ሰላም እንዲኾን፣ የተሻለ ልማት እንዲኖር፣ ሕዝቡ የሚፈልገውን መንግሥታዊ አገልግሎት እንዲያገኝ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። ጽንፈኛ ኃይሉ ወደ ሰላም እንዲመጣ ተጨማሪ እድል ሰጥተን እየሠራን ነውም ብለዋል አሥተዳዳሪው በመግለጫቸው።

አሥተዳዳሪው በጽንፈኝነት እና በሽፍትነት የተሰማሩ ታጣቂዎች ቤተሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሕዝቡ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው በመምከር እና በመገሰጽ ወደሰላም እንዲመጡ ለማድረግ ተጋግዞ መሥራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የሕዝባችን ሰላም እንዲናጋ፣ ልማቱ እንዲስተጓጎል፣ ማኅበራዊ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ አንፈልግም ያሉት አሥተዳዳሪው የሰላም ጥሪውን ችላ ብሎ አሁንም በፀረ ሰላም ኃይልነት እንቅስቃሴ አደርጋለሁ የሚል አካል ካለ ሕግ የማስከበር ሥራችንን እንቀጥላለን ብለዋል። ማኅበረሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች እና ከመንግሥት ጎን ኾኖ ሰላሙን አስጠብቆ እንዲቀጥልም የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላም እጦቱ በገቢ አሠባሠብ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል” የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር
Next article“በደም የተከበረውን በሕግና በላብ ለማጽናት ያለ እረፍት እየሠራን እንገኛለን” አሸተ ደምለው