
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2016 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ ባለፉት ስምንት ወራት መሠብሠብ የተቻለው 572 ሚሊዮን 156 ሺህ ብር ነው። ይህም ከዓመቱ እቅድ ውስጥ 20 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የግብር አወሳሰን፣ አሠባሠብ እና ክትትል ሂደት አሥተባባሪ ታረቀኝ ሞገስ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ቀደም ባሉት ዓመታት ከእቅድ በላይ ገቢ በመሠብሠብ ከራሱ አልፎ ለክልሉ ልማት መፋጠን የጎላ ድርሻ እንደነበረው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ አሁን ላይ ባጋጠመው የሰላም እጦት የነበረውን ከፍታ ማስጠበቅ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰፊ የልማት ፍላጎቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ታረቀኝ የልማት ፍላጎቶቹ የሚመለሱት በሚሠበሠበው ገቢ ልክ በመኾኑ ለገቢ አሠባሠቡ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አሁን ላይ የሰላም ሁኔታው መሻሻል በታየባቸው ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ሥራውን ለማስጀመር የግብር ውሳኔዎችን የማሳወቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!