
አዲስ አበባ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አፈጻጸም የሚዳስስ የፓናል ዉይይት በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ተካሂዷል። ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍ እና የልማት ኤጄንሲ ተዋንያንን በአንድ ላይ በማሠባሠብ መሰረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነቶችን በመለየት የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ እየተተገበረ ያለ ነው።
በፓናል ውይይቱ ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ዲጅታል ኢትዮጵያ በ2025 መተግበር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ አበረታች ውጤቶች እንደተመዘገቡ ገልጸዋል። ስትራቴጂው የበለጠ ስኬታማ እንዲኾን ሚኒስቴር መሥሪያቤታቸው የማስተባበር ተልዕኮውን በአግባቡ እንደሚወጣ ገልጸዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ ሂደት በርካታ ተቋማት ፈጣን እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ያሉት የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬ ሕይዎት ታምሩ ሁሉም ተቋማት ወደ ሥርዓቱ ሊገቡ ይገባልም ብለዋል። በፓናል ውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተገኙ ሲኾን የዘመነች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የዲጅታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን በአግባቡ መገንዘብ እና መተግበር ይገባል ነው ያሉት።
በፓናሉ ከፍተኛ የፌዴራል የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች እና ተጋባዥ እንግዶች የተሳተፉ ሲኾን በዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ አፈጻጸም ላይ ሃሳባቸውን አንፀባርቀዋል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!