
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረ የዝናብ እጥረት ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል፡፡ በተከሰተው ድርቅም በርካታ ወገኖች ለሰብዓዊ ድጋፍ እጃቸውን ዘርግተው ቆይተዋል፡፡ የእንስሳት ሃብት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ የተከሰተው ድርቅ ሰፋ ያለ መኾኑን በተደጋጋሚ ዘግበናል፡፡
የዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደት መልካም የሚባል መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ428 ሺህ በላይ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከመንግሥት እና ከረጂ ድርጅቶች በተገኙ ድጋፎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ወገኖች መካከል 38 ሺህ የሚደርሱ ወገኖችን አሁንም ማዳረስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ግን ሰብዓዊ ድጋፉ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ሲደረግ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ የተሻለ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በተደረገው ድጋፍ የእንስሳትን ሞት መቀነስ ቢቻልም አሁንም የእንስሳት ሞት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ የእንስሳትን ሞት ለመቀነስ ወደ ሌሎች ወረዳዎች የመውሰድ እና በተቻለ መጠን መኖ የማድረስ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ የተከዜን ዳር የመስኖ ልማት በመጠቀም ለእንስሳት መኖ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር መፈጸሙንም ተናግረዋል፡፡
የተሻሉ ወረዳዎችም በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የመኖ ድጋፍ እንዲያደርጉ መሠራቱንም አስታውቀዋል፡፡ ድርቁ እንስሳት ላይ ከፍተኛ አደጋ የደቀነ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ አሁንም ችግር ቢኖርም የተሻለ ድጋፍ መደረጉን እና እየተደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ አሁንም ድጋፍ እንዲደረግላቸው የሚሹ ወገኖች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የእርሻ ወቅት እየደረሰ በመኾኑ ዘር የሚፈልጉ አርሶ አደሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በተለይም በሰሃላ ሰየምት ወረዳ ምንም አይነት ምርት ባለመገኘቱ ሙሉ ለሙሉ ዘር ከመንግሥት ወይም ከረጅ ድርጅቶች ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ እስካሁን ድረስ የነበረው ትኩረት ሰብሰዓዊ ድጋፍ ማድረስ ላይ እንደነበር የተናገሩት ኀላፊው ወደፊት ለአርሶ አደሮች ዘር የማድረስ እና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ ይሠራልም ብለዋል፡፡ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶችን ነድፈው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት፣ ባለሃብቶች፣ ረጂ ድርጅቶች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰላምይሁን ሙላት ዞኑ በጦርነት ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም እየሠራ ባለበት ወቅት የድርቅ ችግር መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ ድርቁ የማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ሥነ ልቡናዊ ስብራት ማስከተሉንም አንስተዋል፡፡
በዞኑ በሥድስት ወረዳዎች ላይ ድርቅ መከሰቱንም አመላክተዋል፡፡ ከ34ሺህ በላይ ሄክታር ሰብል መጎዳቱንም ገልጸዋል፡፡ ድርቁ ውኃ እንዲደርቅ በማድረግ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ የውኃ ችግር እንዲከሰት ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ ድርቁን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴ ጥናት በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ድጋፍ እንዲደረግ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡ የዞኑ አሥተዳደር፣ የክልሉ መንግሥት፣ የፌዴራል መንግሥት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
የሚዲያ ባለሙያዎች፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለተደረገው ድጋፍም አመሥግነዋል፡፡ በዞኑ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 452ሺህ የሚደርሱ ወገኖች ድጋፍ እንደሚፈልጉም አንስተዋል፡፡ ድርቁ ያስከተለው ጉዳት ሰፊ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በተደረገው የቅንጅት ሥራ አብዛኛዎቹን ወገኖች ማዳረስ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ሲደረግ የቆዬው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግ ሽፋን ሲሰጡ የነበሩ ሚዲያዎችም ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከእለት ሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የመልሶ ማቋቋም ሥራ መሥራት ይጠበቃል ያሉት ኀላፊው በቀጣይም ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የእለት ምግብ፣ የዘር እና የማዳበሪያ አቅርቦት ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ባዘጋጀው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ንቅናቄ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የክልሉ መንግሥት የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ካለው ጉዳት አንጻር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በቂ ድጋፍ ለማድረግ የተቸገሩ ወገኖችን በተገቢው መንገድ ለይቶ ማቅረብ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የድጋፍ አቅርቦት መዘግየት መኖሩንም አንስተዋል፡፡ በድርቁ ምክንያት ዜጎች በወረርሽኝ እንዳይጎዱ መሠራቱንም አመላክተዋል፡፡ ድርቅን ፖለቲካ ማድረግ አይገባም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ለተጎዱ ወገኖች ሰበዓዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በድርቅ ምክንያት ሰዎች እንዳይጎዱ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!