
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በየደረጃው ከሚገኙ የፍትሕ አካላት ጋር በመሬት እና መሬት ነክ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ኃይለየሱስ አይዞህበል ከመሬት ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮችን እና ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ቤት የሚመሩ ጉዳዮችን አንስተዋል።
ፕሬዚዳንቱ የሚመለከተው አካል አሥተዳደራዊ ውሳኔዎችን በወቅቱ ባለመወሰኑ እና ውሳኔ ቢሰጥም ባለመፈጸሙ የሚቀርቡ ክርክሮች መበራከታቸውን ጠቅሰዋል። ተገቢውን ውሳኔ ፈጥኖ አለመስጠት ተገልጋዮችን እንደሚያንገላታም ተናግረዋል። አሥተዳደራዊ ውሳኔን ፈጥኖ በመወሰን እና ተከታትሎ ተፈጻሚ በማድረግ ዜጎችን ከእንግልት የሚያድን እና ከክርክሮች የጸዳ አሠራር መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ መሬትን ቅድሚያ ከሦስተኛ ወገን ነጻ ሳያደርግ ለማልማት መሞከር አንዱ ችግር መኾኑንም አንስተዋል። ይህ አይነት ክፍተት ከታየባቸው የከተማ አሥተዳደሩ ልማቶች ውስጥ የባሕር ዳር – ጢስ ዓባይ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክትን እንደ አብነት ጠቅሰዋል። መሬት ለልማት እንዲውል ከተፈለገ በቅድሚያ በሚመለከተው አካል ተወስኖ ለሕጋዊ ባለይዞታዎች ተገቢውን ካሳ መክፈል እና ከሦስተኛ ወገን ነጻ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረውል።
የመንግሥት መሬቶችን በወቅቱ እና በአግባቡ ለክቶ ወደ መሬት ባንክ አሥገብቶ የመጠበቅ ክፍተት ስለመኖሩም አንስተዋል። ይህም ሰዎች የራሳቸው ያልኾነን ይዞታ የራሳቸው አስመስለው አላግባብ በመጠቀም የሕዝብን ጥቅም እያሳጡ እንደኾነ ተናግረዋል። የሰነድ አልባ ይዞታዎችን በመመሪያው መሰረት በወቅቱ በማጣራት መመዝገብ እና መረጃ መስጠት አለመቻሉ የክርክር ምንጭ ስለመኾኑ የባሕር ዳር እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በውይይቱ ላይ ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ውስጥ የገጠር ቀበሌዎችን ጨምሮ የመሬት አሥተዳደር ሕጉን ተከትሎ ሥራዎችን ከማከናወን አኳያ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አመላክተዋል። በከተማው ክልል ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ነዋሪ የኾኑ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በወቅቱ ባለመያዛቸው እና እስካሁንም ያልያዙ በመኖራቸው ትልቅ የመልካም አሥተዳደር ችግር ኾኗል ብለዋል። የአርሶ አደሮች የካሳ እና የትክ መሬት መብት እንዳይረጋገጥ ከማድረጉም በተጨማሪ ለከተማ አሥተዳደሩ ልማትም እንቅፉት ፈጥሯል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
የመንግሥት ይዞታዎችን በአግባቡ መዝግቦ ወደ መሬት ባንክ የማስገባት፣ የማሥተዳደር እና መሰል የመረጃ አያያዝ ክፍተቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል። በዚህም ምክንያት ግለሰቦች የመንግሥት ይዞታዎችን የራሳቸው በማስመሰል እስከፍርድ ቤት ድረስ ሲሄዱ ተስተውሏል፤ አንዳንዴም የሕዝብን እና የመንግሥትን ሃብት ግለሰቦች በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የዛሬው ውይይት ዋና ዓላማ መሬት እና መሬት ነክ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ከፍትሕ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት እና ሕገ ወጥ ተግባራትንም በጋራ ለመከላከል ያለመ ነው ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩም በመሬት ነክ ጉዳዮች ላይ የተደራጀ መረጃ እና ማስረጃ በመያዝ የሕዝብን ሃብት የመጠበቅ እና ለሚመለከተው ዓላማ ብቻ የማዋል ኀላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል ውይይት ነው ብለዋል አቶ ጎሹ። የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
በከተማው ወሰን ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች እና ባለይዞታዎች ማረጋገጫ ደብተር እየተሰጠ ነው ብለዋል። ለሦስት ክፍለ ከተሞች ተሰጥቷል፤ ለቀሪዎችም ለመስጠት ኮሚቴ ተቋቁሟል ነው ያሉት። የካሳ እና ትክ አሰጣጥ ሕግ እና ሥርዓትን መሠረት አድርጎ በመሄድ በኩልም ችግሮች እንደነበሩ ጠቁመዋል። ይህንንም መልክ ለማስያዝ እየተሠራ ነው ብለዋል። ከመሬት ባለይዞታነት ጋር በተያያዘ መብት ያላቸው እንዲከበርላቸው፣ ያላግባብ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱት ደግሞ ተክክለኛ የሕግ ውሳኔ ተሰጥቷቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው “የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱ ለባለመብቶች መብት የሚሰጥ፣ የመንግሥት እና የሕዝብን ሃብትም የሚጠብቅ መኾን አለበት” ሲሉም አስገንዝበዋል። ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡላቸውን ክሶች መረጃ እና ማስረጃን መዝነው የሕዝብ እና የመንግሥትን ሃብት ከመጠበቅ አኳያም ተገቢውን ከለላ መስጠት ሲችሉ ያላግባብ ውሳኔዎች የተወሰኑበት አጋጣሚ እንደነበር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቅሰዋል። እነዚህን ችግሮች በጋራ በመፍታት ውስን የኾነውን የሕዝብ ሃብት መጠበቅ፣ የዜጎችን መብት ማስከበር እና ከእንግልትም ማዳን ይገባል ብለዋል። ለዚህም ከተማ አሥተዳደሩ እና ፍርድ ቤቶች በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!