
ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ የዞኑን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በአማራ ክልል ለወራት በዘለቀው ግጭት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በዚሁ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ ነፍጥ አንስተው ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎች በቀሰቀሱት ግጭት ምክንያት ከደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብት መውደሙን ገልጸዋል።
በዞኑ በተወሰደው የተቀናጀ ሕግ የማስከበር እርምጃ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ተቋርጠው የቆዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን ማስጀመር ተችሏልም ብለዋል፡። በቀጣይም የዞኑን ሕዝብ ሰላም ለማረጋገጥ እና የተቋረጡ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማቶችን ለማስቀጠል ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው፡፡ የዞኑ ሕዝብ ያገኘውን አንፃራዊ ሰላም ሊነጥቅ የሚንቀሳቀስን ማንኛውንም ኃይል እንዲያወግዝም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ ኑርልኝ ዞኑ አሁን ላይ ላገኘው አንፃራዊ ሰላም ትልቅ ዋጋ ለከፈሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እና ለክልሉ የፀጥታ አካላት እንዲሁም ለዞኑ ማኅበረሰብ ያላቸውን አክብሮትም ገልጸዋል፡፡ ከሕግ ማስከበር በተጓዳኝ በዞኑ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ፣ የግብርና ልማት፣ ትምህርት ፣ጤና፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት እና የሥራ እድል ፈጠራ በቀጣይ በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት መኾናቸውንም በመግለጫው አመልክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!