
ወልድያ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉን የሰጠው የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ለማሳለጥ ታላሚ በማድረግ መኾኑን በአማራ ልማት ማኅበር የሰሜን ወሎ ዞን እና አካባቢው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ካሳሁን አምባዬ ገልጸዋል።
ድጋፉ የተማሪዎች የኘላስቲክ ወንበር እና ጠረጴዛ፣ ጥቁር ሰሌዳ፣ ልዩ ልዩ የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ ለመኝታ እና ለመጫወቻ የሚኾኑ ምንጣፎችን ያካተተ ነው። ማኅበሩ ድጋፍ ያደገላቸው ትምህርት ቤቶች በሀብሩ ወረዳ፣ ጉባላፍቶ ወረዳ እና ራያ ቆቦ ወረዳ ለተመረጡ 12 ትምህርት ቤቶች ነው፡፡ድጋፉም በቀጥታ እንደደረሰ ነው ኀላፊው ያስረዱት።
ማኅበሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ ከቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር ለመምህራኑም የሥራ ላይ ሥልጠና እንዲመቻች በማድረግ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን ነግረውናል። የሀራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙሐመድ ይማም እና የመርሳ አባጌትዬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙሐመድ ሁሴን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተማሪዎች ባልተሟላ ግብዓት እየተማሩ መቆየታቸውን ገልጸው ድጋፉ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማሳለጥ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!