ባለፉት ወራት የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በበጀት ዓመቱ ሊሠሩ የታቀዱ ተግባራት አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

19

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ባለፉት ስምንት ወራት የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በበጀት ዓመቱ ሊሠሩ የታቀዱ ተግባራት አፈጻጸም ዝቅተኛ እንዲኾን ማድረጉን ገልጸዋል። አቶ በድሉ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ስምንት ወራት በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋገጥ እና የማስቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራ ማከናዎናቸውን አመላክተዋል።

“ጽንፈኛው ኃይል የፈጠረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ የከተማው ነዋሪዎች ለችግር ተጋልጠዋል” ብለዋል። በዋናነት ደግሞ የግብርና ምርቶች ወደ ከተማዋ በበቂ መጠን እንዳይገቡ በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ማድረጉን ነው አቶ በድሉ ያነሱት። ባለፉት ዓመታት ለደብረብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማደግ የከተማዋ ሰላም መኾን ወሳኝ ሚና እንደነበረውም አንስተዋል። በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት የኢንቨስትመንት ፍሰት እድገቱን ጠብቆ እንዳያድግ ጦርነቱ ተጽዕኖ መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡ የሥራ እድል ፈጠራውም በተመሳሳይ ተጽዕኖ ሥር መውደቁ አመልክተዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።

በበጀት ዓመቱ 24 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ የታቀደ ቢኾነም 19 ኢንዱስትሪዎች ብቻ ወደ ማምረት የገቡ ሲሆን ማሽነሪ መትከል የጀመሩ መኖራቸውንም አመላክተዋል። በበጀት ዓመቱ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ታቅዶ ነበር ያሉት አቶ በድሉ በስምንት ወራቱ አፈጻጸሙ 31 በመቶ ብቻ እንዲኾን የሰላም እጦቱ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም እየታየ በመኾኑ የልማት ሥራዎች በመከናዎን ላይ መኾናቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

የመሬት አያያዝ ሥርዓትን ለማዘመን በተሠራው ሥራ 39 ሺህ ፋይሎችን በቴክኖሎጅ በመታገዝ ማደራጀት መቻሉንም አቶ በድሉ ተናግረዋል። አሠራርን በማዘመን፣ ፈጣን እና ከብልሹ አሠራር የጸዳ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የፀጥታ ችግሩ ባይኖር ኖሮ ከዚህም የተሻለ አፈጻጸም ይኖር እንደነበር አንስተዋል።

በማኅበራዊ ዘርፎች ትምህርት በወቅቱ እና በአግባቡ እንዳይጀመር የፀጥታ ችግር መኖሩ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ነው ያሉት። በጤና ዘርፍ የተሻለ ሥራ መሥራት ቢቻልም የበለጠ ማጠናከር እንዳይቻል የፀጥታው መደፍረስ ምክንያት ስለመኾኑ ጠቁመዋል። አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ተከትሎ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውም ጠቅሰዋል። የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች የሚረጋገጡት አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ነው እና ሕዝቡ ሰላም እንዲረጋገጥ አጋዥ መኾን ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ኤልያሥ ፈጠነ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ዳግም ተመዝግበው ሕጋዊ ኅልውናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ባለሥልጣኑ አሳሰበ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የመካከለኛ ዘመን ግምገማ ወቅት ለዕቅዱ መነሾ የሆኑ ሀገራዊ ተግዳሮቶችን አብራርተዋል።