
አዲስ አበባ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የውይይት መድረክ አካሂደዋል፡፡ ውይይቱ በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ዳግም ያልተመዘገቡ ድርጅቶች እንዲሁም ሕልውናቸውን ማረጋገጥ ያልቻሉ ድርጅቶች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ሕግን በማክበር ታማኝ የኾነ ማኅበርን መገንባት የተቋሙ ዓላማ መኾኑን ጠቅሰዋል። ድርጅቶቹ ሕግን ተከትለው መሥራት የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱንም ነው የተናገሩት፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ባደረገው ክትትል 1 ሺህ 558 ድርጅቶች በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ዳግም እንዲመዘገቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብላቸውም ሊመዘገቡ እንዳልቻሉ አንስተዋል።
296 ድርጅቶች ደግሞ የፋይናንስ ሪፖርታቸውን አለማቅረባቸው ተገልጿል። ድርጅቶቹ ወደ ባለሥልጣኑ ቀርበው አሳማኝ ምክንያት ካላቀረቡ ሊሰረዙ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል፡፡ በመድረኩ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችም ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ውሳኔ ከማሳረፉ በፊት ማኅበራቱ በምን ምክንያት ሪፖርታቸውን ማቅረብ እንዳልቻሉ ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ በውይይቱ አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!