ኅብረተሰቡ ጽንፈኝነትን በመታገል ለአብሮነት እና ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

24

እንጅባራ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ”ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በእንጅባራ ከተማ እያካሄደ ነው።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለሙ ሰውነት ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር እየገጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አመርቂ ድሎችን እያስመዘገበ መኾኑን ተናግረዋል።

በኮንፈረንሱ ፓርቲው በሁለት ዓመት ተኩል ጉዞው ያከናወናቸው የልማት፣ የዲሞክራሲ እና የመልካም አሥተዳደር ሥርዓት ግንባታ ሥራዎች ያሉበት ደረጃ የሚዳሰሱበት እና የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እንደኾነም አቶ አለሙ ገልጸዋል።

በኮንፈረንሱ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ኅብረተሰቡን ለከፍተኛ ቀውስ መዳረጉን ተናግረዋል። የኅብረተሰቡን የመከላከል አቅም እና የፀጥታ ኃይሉን ቅንጅት በመጠቀም ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ከጽንፈኛ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።

የአብሮነት እሴትን የሚሸረሽሩ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን ከወዲሁ ማረቅ ካልተቻለ ማንም አሸናፊ ወደማይኾንበት ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ኅብረተሰቡ ጽንፈኝነትን በመታገል ለአብሮነት እና ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከሕግ ማስከበር ሥራ ጎን ለጎን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል የሽምግልና ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችም መንግሥት የኑሮ ውድነት፣ሥራ አጥ ቅነሳ እና ለመሰል አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። በማጠቃለያ ኮንፈረንሱ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተለያዩ ወረዳዎች እና ከከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የፓርቲው አባላት ተሳትፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዋግ ኽምራ አንጻራዊ ሰላም መኖሩ በልማቱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አግዟል” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር
Next articleየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ዳግም ተመዝግበው ሕጋዊ ኅልውናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ባለሥልጣኑ አሳሰበ።